ትራምፕ በዘንድሮው ምርጫ የሚሸነፉ ከሆነ ድጋሚ ለፕሬዝደንትነት እንደማይወዳደሩ ተናገሩ
የ78 አመቱ አዛውንት በሶስት ተከታታይ ምርጫዎች ሪፐብሊካንን ወከለው እየተወዳደሩ ይገኛሉ
በቅርብ ግዜያት የወጡ አስተያየቶች ትራምፕ በዘንድሮው ምርጫ ሊሸነፉ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ፍንጭ እየሰጡ ነው
የቀድው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዘንድሮ ምርጫ የሚሸነፉ ከሆነ በ2028ቱ ምርጫ ድጋሚ ለፕሬዝደንትነት እንደማይወዳደሩ ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ከመገናኛ ብዙሀን ጋር በነበራቸው ቆይታ በዘንድሮው ምርጫ በካማላ ሃሪስ የሚሸነፉ ከሆነ ቀጣይ የፖለቲካ ጉዞዎት ምን ይመስላል ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡
በምለሻቸውም “ይህ የመጨረሻየ ነው የሚሆነው፥ እንደምናሸንፍ ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን ውጤቶች በተቃራኒ ከሆኑ በቀጣዩም ሆነ ከእርሱ በኋላ በሚመጡ ምርጫዎች ላይ ለፕሬዝዳንትነት አልወዳደርም” ብለዋል፡፡
ትራምፕ የመወዳደር ፍላጎት ቢኖራቸውም አንድ ፕሬዝዳንት ከሁለት የስልጣን ዘመን በላይ እንዳያገለግል የሚያግደው የአሜሪካ ህግ ትራምፕን በ2028 ከመወዳደር የሚገድባቸው ነው፡፡
በተለምዶ በምርጫ እንደሚያሸንፉ ቀድመው በመተንበይ የሚታወቁት ትራምፕ ከቅርብ ግዚያት ወዲህ የዘንድሮውን ምርጫ ሊሸነፉ እንደሚችሉ በተለያዩ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡
ባሳለፍነው ሀሙስ ከእስራኤል አሜሪካውያን ህብረት አባላት ጋር ባደረጉት ስብሰባ በዘንድሮ ምርጫ የሚሸነፉ ከሆነ እስራኤል አሜሪካውያን በከፊል ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋ ነበር፡፡
“ለእኔ ድምጽ የሚሰጡት እስራኤል አሜሪካውያን ከአጠቃላይ ቁጥሩ 40 በመቶ ብቻ ነው። ይህ ማለት 60 በመቶዎቹ ለጠላት ድጋፋቸውን ይሰጣሉ ማለት ነው ይህ መስተካከል አለበት” ሲሉ በስብሰባው ላይ አንስተዋል፡፡
ትራምፕ ሊሸነፉ እንደሚችሉ በቅርቡ በተደጋጋሚ መናገራቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከ2024ቱ ምርጫ እጩነት እራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ በዴሞክራቶች ዘንድ የተፈጠረውን መነቃቃት በመመልከት ሊሆን እንደሚችል ተዘግቧል፡፡
ባይደንን ተክተው የዴሞክራቶች እጩ የሆኑት ካማላ ሃሪስ የፓርቲውን የማሸነፍ እድል በብዙ ቁጥሮች እያሳደጉት እንደሚገኙ እየተነገረላቸው ነው፡፡
ካማላ እና ትራምፕ “ስዊንግ ስቴትስ” በሚባሉት የምርጫውን አሸናፊ በሚወስኑት ግዛቶች ሳይቀር ያላቸው የአሸነፊነት ግምት እጅጉን የተቀራረበ ነው፡፡
የምርጫ ዘመቻ ድጋፍ በማሰባሰብ ደግሞ ዴሞክራቶች አስገራሚ መሻሻሎችን እያሳዩ ነው። ባሳለፍነው ነሀሴ ወር ምክትል ፕሬዝዳንቷ ካማላ 190 ሚሊየን ዶላር ሲያሰባስቡ ትራምፕ ማግኝት የቻሉት 130 ሚሊየን ዶላር ነው፡፡
በቅርቡ ሁለቱ እጩዎች ያደረጉት የምርጫ ክርክር ደግሞ በርካታ መራጮች ወደ ካማላ ሃሪስ እንዲያዘነብሉ ካደረጉ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡
ሆኖም በኢኮኖሚ ፣ በኑሮ ውድነት እና ስደተኝነትን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ትራምፕ አሁንም አብላጫውን ተቀባይነት እንደያዙ ይነገራል፡፡