ትራምፕ በምርጫ ከተሸነፉ አይሁዶችን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ተናገሩ
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ብርቱ ፉክክር በሚደረግባቸው ግዛቶች የአይሁዶችን ድምጽ ማግኘትን ትልቅ ጉዳይ አድርጎታል
ትራምፕ ምርጫውን የሚሸነፉ ከሆነ እስራኤል በሁለት አመት ውስጥ ትጠፋለች ሲሉ ተናግረዋል
ትራምፕ በምርጫ ከተሸነፉ አይሁዶችን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ተናገሩ።
የሪፐብሊካን ፕሬዝደንታዊ እጩ የሆኑት የቀድሞው ፕሬዝደንት ድናልድ ትራምፕ በመጭው ጥቅምት ወር መጨረሻ የሚካሄደውን ምርጫ በዲሞክራት እጩዋ ካማላ ሀሪስ የሚሸነፉ ከሆነ የአይሁድ አሜሪካውያን መራጮችን በከፊል ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በእስራኤል-አሜሪካውያን የብሔራዊ ምክርቤት ስብሰባ ላይ የተገኘት ትራምፕ ሀሪስ በአሜሪካ አይሁዶች ድጋፍ እየመሯቸው መሆኑን በቅሬታ አሰምተዋል። ትራምፕ ሀሪስ ምርጫውን የሚያሸንፉ ከሆነ እስራኤል እንደምትጠፋ እና ለዚህም ዲሞክራቶችን የመምረጥ ዝንባሌ ያሳዩት አይሁዶች በከፊል ተጠያቂ ይሆናሉ ሲሉ ሞግተዋል።
ትራምፕ ለተሰበሰበው ህዝብ "60 በመቶ የሚሆነው መራጭ ጠላትን ከመረጠ እና ይህን ምርጫ ከተሸነፍኩ የአይሁድ ህዝብ ችግር ይገጥመዋል፤ እስራኤል በሁለት አመት ውስጥ ትጠፋለች" ብለዋል ። ትራምፕ ሀሪስ በአይሁድ መራጮች ውስጥ 60 በመቶ እመሩ መሆናቸዉን የሚያሳይ የህዘብ አስተያየትን(ፖል) ጠቅሰዋል።
ትራምፕ ባሸነፉበት የ2016 ምርጫ እና በተሸነፉበት የ2020 ምርጫ ከ30 በመቶ በታች የአይሁዶችን ድምጽ ማግኘታቸው ቅር እንዳሰኛቸው ገልጸዋል። የቀድሞ ፕሬዝደንት የጠቀሱት የህዝብ ድጋፍ የትኛውን እንደሆነ ባይጠቅሱም፣ የፔው ረሰርች የቅርብ መረጃ የአሜሪካ አይሁዶች ከትራምፕ ይልቅ ሀሪስን እንደሚመርጡ አሳይቷል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ብሎ በተካሄደ ጉባኤም በአሜሪካ ውስጥ ጸረ-ጽዮናዊነትን(ጸረ-አይሁድ) በጽኑ እንደሚታገሉ ተናግረዋል። የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ብርቱ ፉክክር በሚደረግባቸው ግዛቶች የአይሁዶችን ድምጽ ማግኘትን ትልቅ ጉዳይ አድርጎታል።
ለአስርት አመታት በተካሄዱ የፌደራል ምርጫዎች የአሜሪካ አይሁዶች ለዲሞክራቶች ያዘነብላሉ፤ ነገርግን በአይሁዶች ድምጽ ሊኖር የሚችል የተወሰነ ለውጥ የመጭውን ምርጫ አሸናፊ ይወስናሉ።
ለምሳሌ ፕሬዝደንት ባይደን የ2020ውን ምርጫ በ81ሺ ድምጽ ባሸነፉባት ብርቱ ፉክክር በሚካሄድባት ፔንሲልቫንያ ግዛት 400ሺ አይሁዶች ይኖራሉ።
የሀሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ቃል አቀባይ ሞርጋን ፊንኬልቲን ትራምፕ ጸረ-ጺዮናዊ ናቸው የሚል ትችት ሰንዝረዋል። ትናንት ባሰሙት ንግግር አይሁድ አማች እንዳላቸው ያስታወሱት ትራምፕ ጸረ-ጺዮናዊ ናቸው የሚለውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።