ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን ለመንግስት ለማስመለስ ያስችላል የተባለው አዋጅ በፓርላማው ጸደቀ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን በሶስት ተቃውሞ እና በአራት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል
አዋጁን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በዜጎች እና በባለሃብቶች ላይ ስጋት የሚፈጥር አሰራር እንዳይኖር ጥንቃቄ እንዲደረግ የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል
ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን ለመንግስት ለማስመለስ ያስችላል የተባለው አዋጅ በፓርላማው ጸደቀ።
14ኛ መደበኛ ስብሰባው ያካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅን በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ የነበረው አዋጅ ግለሰቦች በወንጀልና በሙስና እንዲሁም ሌሎች ምንጫቸው ባልታወቁ መንገዶች ያፈሩትን ንብረት የሚያስመልስ ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም አዋጁ 10 ዓመት ወደኃላ በመሄድ የመንግስትና የህዝብ ንብረትን የሚያስመልስ የሕግ-ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱ በረቂቅ አዋጁ የተደረጉ ማስተካከያዎችና የተጨመሩ አንቀጾችን እንዲሁም ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ሰብሳቢዋ ረቂቅ አዋጁ በወንጀል የተገኘ ንብረትና ገንዘብን ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳደር የሚያስችል ግልጽና ዝርዝር የንብረት ማስመለስና የማስተዳደር ሥርዓት መዘርጋትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የንብረት ማስመለስ እና መውረስ መሰረታዊ ድንጋጌዎች ወጥ የሆነ ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት በንብረት ማስመለስና መውረስ ሂደት ውስጥም ሆነ ንብረቱ ከተወረሰ በኋላ የንብረቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
ያለ አግባብ በግለሰብ፣ በዘመድ አዝማድና ሌሎች ሰዎች ስም የተደበቀ የመንግስት እና የህዝብ ሀብትና ንብረት ለማስመለስ ከዚህ ቀደም የነበረውን የህግ ክፍተት አዋጁ እንደሚሞላ ተነግሮለታል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በአዋጁ ላይ በአስረጅ፣ በህዝብና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ግብዓት እንደሰበሰበ አክለው ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ሕገ ወጥ የሆነ ሀብትን በዘመድ አዝማድ የተደበቀ፣ የተሸሸገና ምንጩ ያልታወቀ የሀገር ሃብት ወደ ኋላ ሂዶ ለማስመለስ አዋጁ ሚና እንደሚኖረው መናገራቸውን ከምክር ቤቱ ይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል አዋጁን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በዜጎች እና በባለሃብቶች ላይ ስጋት የሚፈጥር አሰራር እንዳይኖር ጥንቃቄ እንዲደረግ ፤የፍትህ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡
ምክር ቤቱ የቀረበለትን የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1364/2017 አድረጎ በሶስት ተቃውሞ ፣በአራት ድምፅ ተአቅቦ ፣ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ ምክር ቤቱ የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ሥርዓት ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ አጽድቋል፡፡
ነዳጅ መንግሥት ከተመነው የመሸጫ ዋጋ በላይ ሲሸጡ የተገኙ ነጋዴዎች እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር እንዲቀጡ የሚደነግገው አዋጅ ፤ ድርጊቱ በተደጋጋሚ ከተፈጸመ የገንዘብ መቀጮው ላይ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣትን አካቷል፡፡
የነዳጅ ምርቶችን ሆን ብሎ ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ማቅረብ ከአምስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እሥራት እና ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ በአዋጁ ላይ ተቀምጧል፡፡