እስራኤል ከቱርክ ጋር ጦርነት ውስጥ ልትገባ የምትችልበት እድል መኖሩን የእስራኤል የደህንነት አማካሪ ኮሚሽን አስታወቀ
ኮሚሽኑ በአንካራ የሚደገፉ የሶሪያ ቡድኖች ከኢራን ጋር ካለው ግጭት የበለጠ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ ብሏል
በተጨማሪም በ2025 ቴልአቪቭ 70 በመቶ ወታደራዊ አቅሟን ከመከላከል ወደ ማጥቃት አቋም ልትቀየር እንደሚገባ ሪፖርቱ መክሯል
ቱርክ በሶሪያ ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ቡድኖች በምታደርገው ድጋፍ ምክንያት እስራኤል ከአንካራ ጋር ጦርነት ውስጥ የምትገባበት እድል መኖሩን የመንግስት ደህንንት አማካሪ ኮሚሽን አሳሰበ።
በነሐሴ 2024 በእስራኤል መንግስት የደህንነት ጉዳዮችን ለማማከር የተቋቋመው የናጌል ኮሚሽን የሀገሪቱን የጸጥታ እና ደህንነት ምስል የሚያሳይ ሰፊ ሪፖርት አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑን የሚመሩት የቀድሞ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ሀላፊ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የነበሩት ፕሮፌሰር ጃኮብ ናጌል ናቸው።
ሪፖርቱ አንዳንድ የሶሪያ ቡድኖች ከቱርክ ጋር ያላቸው ትብብር አደገኛነት በማጉላት፤ አንካራ በመካከለኛው ምስራቅ የኦቶማን ዘመን ተጽእኖን ወደነበረበት ለመመለስ ምኞት እንዳላት ገልጿል፡፡
በዚህም ከሶሪያ የሚመጣው ስጋት በበሽር አላሳድ መንግስት ከነበረው እና ኢራን ከምትፈጥረው ስጋት የበለጠ አደገኛ ሊሆን ይችላል ብሏል።
በተጨማሪም የእስራኤል የመከላከያ ስትራቴጂ ከመከላከል ይበልጥ ንቁ ርምጃ ወደ መውሰድ እንዲቀየር መክሯል፡፡
ይህ የስትራቴጂ ለውጥ 70 በመቶ ወታደራዊ አቅሟን ወደ ማጥቃት ተግባር መቀየር እና የ2025 የመከላከያ በጀትን በ9 ቢሊየን ሼክል (2.5 ቢሊየን ዶላር) መጨመርን ሊያካትት አንደሚገባ ተናግሯል፡፡
በዚህ አመት የሀገሪቱ አጠቃላይ ወታደራዊ በጀት ወደ 34 ቢሊየን ዶላር ማደግ አለበት ያለው ኮሚሽኑ እስከ 2030 ወታደራዊ ወጪዋን እያሳደግች መቀጠል እንደሚኖርባት ነው ያሳሰበው፡፡
በ2024 መጨረሻ በሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) በተባለው ቡድን በተመራው ጥቃት የበሽር አላሳድ መንግስት መውደቅ በአንካራ እና ደማስቆ በኩል አዲስ ወዳጅነት እንዲያብብ ስለማድረጉ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ይህ ወዳጅነት እያደገ መምጣት የእስራኤል ብሔራዊ ደህንነት ላይ አደጋ ሊፈጥር መቻሉ አንካራ እና ቴልአቪቭን ጦር ሊያማዝዝ እንደሚችል አርቲ ሪፖርቱን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የቱርክ ባለስልጣናት ለአዲሱ የሶሪያ አመራር በመልሶ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። በደማስቆ ላይ የተጣሉ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችም እንዲነሱ እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡
በተጨማሪም አንካራ ከአዲሱ የሶሪያ አስተዳደር ጋር በመሆን በኩርድ ታጣቂዎች ላይ የጋራ ዘመቻን ለማከናወን መስማማታቸው ተገልጿል።
እስራኤል በበኩሏ የአሳድ መወገድን ተከትሎ የተለያዩ ከፍተኛ የጦር መሳሪያዎች በተሳሳቱ እጆች እንዳይወድቁ በሚል በሶሪያ ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች እና ከፍተኛ የጦር መሳሪያወችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ፈጽማለች፡፡
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረበት ከጥቅምት 2023 ወዲህ የእስራኤል እና የቱርክ ግንኙነት በውጥረት የተሞላ ሆኗል፡፡
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶሀን እስራኤልን “በመንግስታዊ ሽብርተኝነት” እና “የዘር ማጥፋት ወንጀል” በመፈጸም ወንጅለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አንካራ በህዳር ወር ከእስራኤል ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስታቋርጥ ቴልአቪቭ በበኩሏ ሀገሪቱ ለሀማስ የምታደርገውን ድጋፍ አውግዛለች፡፡