አሜሪካ ከዩክሬን ጦርነት የምትወጣበት ግልጽ የሆነ ስትራቴጂ ያስፈልጋታል - ዶናልድ ትራምፕ
የሪፐብሊካኑ እጩ ዋሽንግተን በአፍጋኒስታን የገጠማት “ውርድት” በዩክሬን እንዳይደገም እሰጋለሁ ሲሉ ተናግረዋል
ትራምፕ በዘንድሮው ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ጦርነቱን በፍጥነት እንደሚያስቆሙ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዴሞክራቶች አስተዳደር በዩክሬን የማያሸንፈውን ጦርነት እየተዋጋ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
ጆ ባይደን በማያሸንፈው ጦርነት ውስጥ የአሜሪካውያንን ታክስ ከፋዮች ገንዘብ በከንቱ እያባከነ ነው ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ በጆርጂያ በነበራቸው የምርጫ ቅስቀሳ መድረክ ባደረጉት ንግግር አሜሪካ እንደ አፍጋኒስታን ጦርነት ሌላ ለረጅም አመት የምትቆይበት ግጭት ውስጥ እራሷን እየከተተች ነው ብለዋል፡፡
“ባይደን እና ካማላ የማንወጣው ፣ አሜሪካውያንን ብዙ ገንዘብ የሚያስወጣ ፣ በማናሸንፈው ጦርነት ውስጥ ከተውናል፡፡ በእርግጠኝነት ከዚህ ጦርነት እንዴት እንደሚወጡ ምንም አይነት ስትራቴጂ የላቸውም” በሚል ወቅሰዋል ፡፡
በተጨማሪም የሩሲያን ጦርነት የማሸነፍ ልምድ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ “ሂትለርን አሸንፋለች ናፖሊዮንም ጥለዋለች። ይህንን ጦርነት የምታሸነፍ ከሆነ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ከባድ ነው” ሲሉ ነው ያስጠነቀቁት
ከዚህ ቀደም በ2024ቱ ምርጫ ቢያሸንፉ የዩክሬን- ሩሲያን ጦርነት በ24 ሰአታት ውስጥ እንደሚያስቆሙ ሲናገሩ የተደመጡት ትራምፕ በዚህኛው ንግግራቸውም ፕሬዝዳንት የሚሆኑ ከሆነ ሁለቱን ተዋጊዎች በማደራደር ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ ቃል ገብተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የሚገኙት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “የማሸንፊያ እቅድ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ጫናዎችን ማሳደር ይችላል ያሉትን እቅድ ለባይደን እና ካማላ ሃሪስ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡
ዘለንስኪ በዚህኛው ዙር ጉብኝታቸው ከአሜሪካ ተጨማሪ የ375 ሚሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማዕቀፍ ያገኛሉ ተብሏል፡፡
የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማዕቀፉ ሚሳይሎች ፣ በተዋጊ ጄቶች ጥቅም ላይ የሚውሉት ክላስተር ቦምቦች እና ሌሎች የከባድ ጦር መሳርያ ተተኳሾች የተካተቱበት እንደሆነ አርቲ ዘግቧል፡፡
የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ከተጀመረበት የካቲት 2022 ጀምሮ ዋሽንግተን ለኪቭ 56 ቢሊየን ዶላር ግምት ያላቸው የጦር መሳሪያዎችን ቀጥተኛ ድጋፍ አድርጋለች፡፡
በተጨማሪም ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ለዩክሬን 61 ቢሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግ በኮንግረሱ ጸድቋል፡፡