በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተኮሰው ሰው ቀደም ብሎ ድሮን አብርሮ ነበር ተባለ
ዶናልድ ትራምፕ ከ130 ሜትር ርቀት ከተተኮሰባቸው ጥይት በተዓምር መትረፋቸው ይታወሳል
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት ተቋም ሀላፊ ሃላፊነቱን አልተወጣም በሚል ስልጣን እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው ይገኛል
በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተኮሰው ሰው ቀደም ብሎ ድሮን አብርሮ ነበር ተባለ፡፡
የፊታችን ህዳር ወር ላይ በሚካሄደው ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው ቅዳሜ የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ እያሉ በተተኮሰባቸው ጥይት ቆስለው ወደ ህክምና መግባታቸው ይታወሳል።
ለጥቂት ከሞት የተረፉት ዶናልድ ትራምፕ በፔንሲልቫኒያ ግዛት ለደጋፊዎቻቸው ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ ነበር ማቲው ክሩክስ በተሰኘ የ20 ዓመት ወጣት በጥይት የቆሰሉት።
ማቲው ክሩክስ በ130 ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ ስናይፐር በተሰኘ የጦር መሳሪያ ዶናልድ ትራምፕን ተኩሶ አቁስሏቸዋል፡፡
የሀገሪቱ ሚስጢራዊ የደህንነት ተቋም ሰራተኞች ወዲያውኑ በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ ማቲው የተገደለ ሲሆን ጉዳዩ አሁንም በአሜሪካ እና በመላው ዓለም ትኩረት እንደሳበ ይገኛል።
ቢቢሲ የአሜሪካ ብዙሃን መገናኛዎችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ማቲው ክሩክስ ዶናልድ ትራምፕ ንግግር በሚያደርጉበት ቦታ ለይ አስቀድሞ ድሮን አብርሮ ነበር ተብሏል፡፡
ተጠርጣሪው ድሮን ያበረረው ግድያውን ለማሳካት ስለ ስፍራው በቂ መረጃ ለማግኘት በሚል ሊሆን እንደሚችል በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ስለ ዶናልድ ትራምፕ የግድያ ሙከራ በየጊዜው አዳዲስ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን ከቀናት በፊት የማቲው አባት ልጃቸው የተለየ ባህሪ ማሳየቱን ተከትሎ ፖሊስ ክትትል እንዲያደርግ ከክስተቱ በፊት ሪፖርት አድርገው እንደነበር መገለጹ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪም ለዶናልድ ትራምፕ ድጋፍ ለማድረግ ወደ መድረኩ የመጡ ሰዎች ወጣቱ የጦር መሳሪያ ይዞ ማየታቸውን እና ሁኔታውን ወዲያውኑ ለፖሊስ አሳውቀው እንደነበር ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም የሀገሪቱ ሚስጢራዊ ደህንነት ጥበቃ ክፍል ሀላፊ እና የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሀላፊ ሀላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል ስልጣን እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው ይገኛል ተብሏል።