ዶናልድ ትራምፕ ከቢሊየነሮች ዝርዝር የወጡት የትሩዝ የአክሲዮን ዋጋ በመቀነሱ ነው
የቀድሞ አሜሪካ ፐሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከብሉምብርግ የቢሊየነሮች ዝርዝር ውጪ መሆናቸው ተነግሯል።
በድጋሚ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆን በመፎካከር ላይ የሚገኙት ዶናልድ ትራምፕ ከብሉምበርግ 500 ቢሊየነሮች ዝርዝር መሰረዛቸው ታውቋል።
ዶናልድ ትራምፕ ከብሉምበርግ ቢሊየነር ዝርዝር ውጪ የተደረጉት ትሩዝ የሚል መጠሪያ ያለው የምህበራዊ ትስስር ገጻቸውን የሚያስተዳድረው ትራምፕ ሚዲያ የአክሲዮን ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ ነው።
የትሩዝ ሶሻል ማህበራዊ ትስስር ገጽ ባለቤት ትራምፕ ሚዲያ የአንድ አክሲዮን ዋጋ 78 ዶላር የነበረ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ቀን ግብይቱም በ57.99 ዶላር ነበር የተጠናቀቀው።
ባሳለፍነው ረቡዕ ደግሞ የአክሲዮን ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ በ36 ዶላር መሸጡን እና ይህንን ተከትሎም ትራምፕ ከ500 ቢሊየነሮች ዝርዝር መውጣታቸው ተነግሯል።
የአክስዮን ዋጋው መውረድ የዶናልድ ትራምፕ ሃብት ባሳለፍነው መጋት ወር ከነበረበት 7.85 ቢሊየን ዶላር ወደ 4.7 ቢሊየን ዶላር እንዲወርድ ማድረጉም ነው የተገለጸው።
ዶናድ ትራምፕ የሚመሩት ትራምፕ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ ቡድን (ቲ.ኤም.ቲ.ጂ) 'ትሩዝ ሶሻል' የተባለ አዲስ ማኅበራዊ ሚዲያን ከሁለት ዓመት በፊት በፈረንጆቹ 2022 ላይ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የቀዶሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ 2021 ጥር ወር ከዋሽንግተን ዲሲው የካፒቶል ሂል ጥቃት ጋር በተያያዘ ከትዊተር፣ ፌስቡክ እና ዩትዩብ መታገዳቸውን ተከትሎ ነበር የራሳቸውን ማህበራዊ ትስስር ገጽ የከፈቱት።