ሩሲያ "የዩክሬኑን ጦርነት በአንድ ቀን አስቆመዋለሁ" ለሚሉት ትራምፕ ምላሽ ሰጠች
ትራምፕ በሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ክብር የሚቸረው "ትክክለኛ ፕሬዝደንት" በአሜሪካ ቢኖር ኖሮ፣ ሞስኮ ዩክሬንን አትወርም ነበር ይላሉ
የሩሲያ የተመድ አምባሳደር ቫሳሊ ነቤንዚያ " የዩክሬንን ቀወስ በአንድ ቀይ አይፈታል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል
ሩሲያ "የዩክሬኑን ጦርነት በአንድ ቀን አስቆመዋለሁ" ለሚሉት ትራምፕ ምላሽ ሰጠች።
በድጋሚ ከተመረጡ "የዩክሬኑን ጦርነት በአንድ ቀን አስቆመዋለሁ" ስለሚሉት የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እጩ ተወዳዳሪ ትራምፕ የተጠየቁት፣ የሩሲያ የተመድ አምባሳደር ቫሳሊ ነቤንዚያ " የዩክሬንን ቀወስ በአንድ ቀን አይፈታም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የሪፐብሊካን እጩ የሆኑት ትራምፕ በሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ክብር የሚቸረው "ትክክለኛ ፕሬዝደንት" በአሜሪካ ቢኖር ኖሮ፣ ሞስኮ በፈረንጆቹ የካቲት 2022 ዩክሬንን አትወርም ነበር ይላሉ።
"ተመርጭ ወደ ቢሮ ከመግባቴ በፊት በጥር 20ዎቹ በፑቲን እና በዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ መካከል ያለው ጦርነት እልባት እንዲያገኝ አደርገዋለሁ። ጦርነቱን አስቆመዋለሁ" ሲሉ ትራምፕ ከዲሞክራቱ ፕሬዝደንት ባይደን ጋር ባለፈው ሳምንት በሲኤንኤን ቴሌቪዥን ቀርበው በተከራከሩበት ወቅት ተናግረዋል።
የአሜሪካ መራጮች ሀገሪቱን ለቀጣይ አራት አመታት የሚመራትን ፕሬዝደንት ለመምረጥ በፈረንጆቹ ህዳር አምስት ድምጽ ይሰጣሉ።
ሩሲያ የምርጫው ውጤት በእሷ ላይ ሊኖር የሚችለውን ተጽእኖ ልታጣጥል ብትሞክርም፣ ዋሽንግተን ከሞስኮ ጋር እየተዋጋች ላለችው ዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ስለሚወሰን ውጤቱ ተጽእኖ ይኖረዋል።
አምባሳደር ንቤንዚያ የሩሲያን የሐምሌ ወር የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝደንትነት ለማስጀመር በሰጡት መግለጫ" የዩክሬን ቀውስ በአንድ ቀን አይፈታም"ብለዋል።
ለዚህ ምላሽ የሰጡት የትረምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቃል አቀባይ ሰቴቨን ችንግ "ትራምፕ በታሪክ የተዋጣለት መሪ እና አደራዳሪ ነው፤ከተመረጠ ይህን ግጭት ይፈታዋል" ብለዋል።