ትራምፕ ከአሜሪካ ኮሌጆች ለሚመረቁ የውጭ ሀገር ተማሪዎች ግሪን ካርድ እሰጣለሁ አሉ
የአወዛጋቢው የቀድሞ ፕሬዝዳንት አስተያየት ከስደተኛ ጠል አቋማቸው የተቃረነ ነው ተብሏል
የትራምፕ ተፎካካሪ ባይደንም አሜሪካዊያንን ላገቡ የውጭ ሀገር ዜጎች ከላላ የሚሰጥ ፖሊሲ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድጋሚ ከተመረጡ በአሜሪካ ኮሌጆች ለሚመረቁ የውጭ ሀገር ዜጎች ግሪን ካርድ እንደሚሰጡ ቃል ገቡ።
ህገወጥ ስደተኞችን “እንሰሳት ናቸው፤ ደማችን እየበከሉት ነው” በማለት እስከመዝለፍ የደረሱት ትራምፕ ከቀደመው አቋማቸው የተቃረነ አስተያየት የሰጡት “ዘ ኦል ኢን ፖድካስት” ላይ ቀርበው ባደረጉት ቃለምልልስ ነው።
“በአሜሪካ ኮሌጆች ሁለት አመትም ይሁን አራት አመት ተምረው የሚመረቁ ተማሪዎች በሀገሪቱ መቆየት ከፈለጉ ሊከለከሉ አይገባም፤ ከዲፕሎማቸው ጋር ግሪን ካርድ ወዲያውኑ እንዲያገኙ አደርጋለሁ” ነው ያሉት ዶናልድ ትራምፕ።
ግሪን ካርድ በአሜሪካ በቋሚነት መኖርና መስራት የሚያስችል ሲሆን፥ የሀገሪቱን ዜግነት ለማግኘትም ትልቅ ድርሻ አለው።
አወዛጋቢው ፕሬዝዳንት በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች ተምረው ለሚመረቁ የሌሎች ሀገራት ዜግነት ያላቸው ተማሪዎች ግሪን ካርድ ለመስጠት ቃል የገቡት እውቀትና ክህሎታቸውን በአሜሪካ ለማስቀረት ነው።
“ከሃርቫርድ፣ ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ስመገናና ኮሌጆች የሚመረቁ ተማሪዎችን የመኖሪያና የስራ ፈቃድ በመንፈግ ስናጣቸው እጅግ ያሳዝናል” ብለዋል ትራምፕ።
ተምረው በተመረቁባት አሜሪካ መኖርና መስራት ያልተፈቀደላቸው የቻይና እና ህንድ ዜግነት ያላቸው ተማሪዎች ወደሀገራቸው ተመልሰው ቢሊየነሮች መሆናቸውንና በሺዎች ቀጥረው እያሰሩ መሆኑን በመጥቀስም እድሉን ሰጥተን አሜሪካን ለማሳደግ ልንጠቀምባቸው ይገባል ሲሉም አብራርተዋል።
የትራምፕ ምክረሃሳብ በየአመቱ የአሜሪካ ዜግነት የሚጠይቁ ሰዎችን ቁጥር በመቶ ሺዎች ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ሲኤንኤን ዘግቧል።
ስደተኛ ጠሉ ፖለቲከኛ በህዳር ወር በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸንፈው ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት ከገቡ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ወደሀገራቸው እንደሚመልሱ ሲዝቱ ቆይተዋል።
በምርጫ ቅስቀሳቸውም ተቀናቃኛቸውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በስደተኞች ላይ የተለሳለሰ አቋም ይዘዋል በሚል ሲከሷቸው ነበር።
የ78 አመቱ ፖለቲከኛ በ“ዘ ኦል ኢን ፖድካስት” ላይ የሰጡት አስተያየት ያልተጠበቀ ይምሰል እንጂ ለዴሞክራቱ ባይደን የሰሞኑ ፖሊሲ ምላሽ ነው ተብሏል።
ባይደን አሜሪካዊ ዜጋ ያገቡና ህጋዊ የመኖሪያ ሰነድ ለሌላቸው ሰዎች ከለላ የሚሰጥ ፖሊሲ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
አዲሱ ፖሊሲ አሜሪካውያንን ያገቡና ሰነድ አልባ የውጭ ዜጎች በአሜሪካ ህጋዊ ቋሚ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ ለማግኘት ከአሜሪካ ሳይወጡ ጥያቄ ማቅረብ እንዲያስችሉ የሚያደርግ ነው።
ይህ ከ500 ሺህ በላይ ህገወጥ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ተጠርንፎ ከመመለስ የሚታደገው ውሳኔ ከሪፐብሊካኖች ጋር በሚተናነቁባቸው ግዛቶች ድምጽ ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ይጠበቃል።
የትራፕም ለተማሪዎች ከዲግሪ ወይም ዲፕሎማቸው ጋር ግሪን ካርድ እንሰጣለን አስተያየትም ከወጣቶችና ስደተኞች ድምጽ ለማግኘት ያለመ መሆኑ ተገምቷል።