ድምጹ ብቻ የሚያሸብረው የሩሲያው “ቲዩ-95” ቦምብ ጣይ አውሮፕላን
ዩክሬን ሚሳኤልና ቦምብ ተሸካሚው ግዙፍ አውሮፕላን ወደ ግዛቷ ሚሳኤሎችን መተኮስ መጀመሩን አስታውቃለች
ከ1956 ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው “ቲዩ-95” ሳያርፍ ከ13 ሺህ በላይ ኪሎሜትሮችን መጓዝ ይችላል
“ገዳዩ የኒዩክሌር ቦምብ ጣይ አውሮፕላን” የሚለው የሩሲያውን ““ቲዩ-95” ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በአጭሩ ይገልጸዋል።
ዩክሬንም ዛሬ ማለዳ ይህ አውሮፕላን ከደቡብ ምዕራብ ሩሲያ ኤግልስ የአየር ማዘዣ ተነስቶ ወደግዛቴ ጉዞ ጀምሯል ብላለች።
የአየር መቃወሚያ ስርአቷ በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅ ያዘዘችው ኬቭ፥ ከቦምብ ጣይ አውሮፕላኑ የተወነጨፉ ሚሳኤሎች በስአታት ውስጥ ወደ አየር ክልሏ እንደሚደርሱ ገልጻለች።
“ቲዩ-95” የጦር አውሮፕላን ለምን አስፈሪ ሆነ?
ግዙፉ ስትራቴጂክ ኒዩክሌር ቦምብ ጣይ አውሮፕላን አራት ሞተሮች ያሉት ሲሆን፥ ክሩዝ ሚሳኤሎች እና አውዳሚ ቦምቦችን መሸከምና ማስወንጨፍ ይችላል።
የአቪየሽን ባለሙያዎች እንደሚሉት “ቲዩ-95” ሶቪየብ ህብረት ከሰራቻቸው ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ሁሉ ስኬታማው ነው።
በተርባይን ሞተር ከሚንቀሳቀሱ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ውስጥም ፈር ቀዳጅና ተመሳሌት መሆኑንም ነው የአሜሪካው ጋዜጣ ዘ ናሽናል ኢንተረስት ያስነበበው።
በ1950ዎቹ መጀመሪያ “ቱፖሌቭ” በተሰኘ ተቋም ዲዛይኑ የተሰራለት “ቲዩ-95” ከ1956 ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ነው። በአሁኑ ወቅትም የሩሲያ አየር ሃይል ይህን ግዙፍ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ለተለያዩ ወሳኝ ግዳጆች ይጠቀማል።
የሩሲያው “ቲዩ-95” ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ዲዛይን የተሰራው በኦስትሪያው የአቪየሽን ተመራማሪ ፈርዲናንድ ብራንድኔር በተመራ ጀርመናውያን መሃንዲሶች ቡድን ነው።
12 ሺህ የፈረስ ጉልበት ያላቸውን የአውሮፕላኑን ተርባይን ሞተሮች የሰሩት ባለሙያዎች በሩሲያ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ ጀርመናውያን ናቸው።
“ቲዩ-95” አራት ቱርባይን ሞተሮቹ የጄት ሞተር ከሚጠቀሙት በተሻለ ረጅም ርቀት እንዲጓዝ ያደረገው ሲሆን፥ ሳያርፍ ከ13 ሺህ ኪሎሜትሮች በላይ መብረር ይችላል ተብሏል።
ግዙፉ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን የሚሸከመው የጦር መሳሪያ ብቻ ሳይሆን ድምጹም የሚያሸብር ነው፤ በሰማይ ላይ እየበረረ በባህር ሰርጓጅ መርከቦች ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ጭምር ይሰሙታል።
ሩሲያ በፈረንጆቹ 2015 በሶሪያ የአይኤስ የሽብር ቡድን ላይ ጥቃት ማድረስ ስትጀምር “ቲዩ-95” ጥቅም ላይ መዋሉ ይታወሳል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ይህን የሰማይ ላይ አሸባሪ እስከ 2040 ድረስ አገልግሎት እየሰጠ እንዲቆይ ማቀዱም ተዘግቧል።
ሩሲያ ምን ያህል “ቲዩ-95” አውሮፕላኖች አሏት? የአሜሪካ ፉክክርስ?
ሩሲያ 55 “ቲዩ-95” ቦምብ ጣይ አውሮፕላን እንዳላት መረጃዎች ያሳያሉ።
ዘ ናሽናል ኢንተረስት ጋዜጣ እንዳስነበበው ይህ አውሮፕላን ከአሜሪካው “ቢ-52” ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ጋር የሚፎካከር ነው።
በቀዝቃዛው ጦርነት የተሰጣቸው ተልዕኮ፣ የመጫን አቅም እና ለረጅም አመታት አገልግሎት መስጠት የሁለቱ ሀያላን ሀገራት ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን ያመሳስላቸዋል።
አሜሪካ 72 “ቢ-52” የኒዩክሌር ቦምብ መጣል የሚችሉ አውሮፕላኖች አሏት።