SR-72 አውሮፕላን በፈረንጆቹ በቀጣዩ 2025 የመጀመሪያ በረራውን ያደርጋል
የሎክሄድ ማርቲን ከፍተኛ ሚስጥራዊ ሃይፐርሶኒክ አውሮፕላን SR-72 ወይም “ሰን ኦፍ ብላክ በርድ” የዓለማችን ፈጣኑ አውሮፕላን ማዕረግን ሊቀዳጅ እንደተቃረበ ተነግሯል።
SR-72 “ሰን ኦፍ ብላክ በርድ” አውሮፕላን በሰዓት እስከ 6 ሺህ 437 ኪሎ ሜትር መክነፍ ችሏል የተባለ ሲሆን፤ ይህም የዓለማችን ፈጣኑ አውሮፕላን እንደሚያደርገው ነው የሚጠበቀው።
አውሮፕላኑ SR-71 “ብላክ በርድ” ተከታይ ነው የተባለ ሲሆን፤ SR-71 በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ወሳኝ የጦር አውሮፕላን እንደነበረ ይነገርለታል።
SR-71 “ብላክ በርድ” የጦር አውሮፕላን በፈረንጆቹ 1974 ወደ አገልግሎት የገባ ሲሆን፤ በወቅቱም የዓለማችን ፈጣን አውሮፕላን የሚል ክብረወሰንን ተቀዳጅቷል።
SR-71 በፈረንጆቹ በ1998 በአሜሪካ አየር ኃይል ከአገልግሎት እንዲወጣ የተደረገ ቢሆንም በፈጣንነቱ ግን እስካሁን ተወዳደሪ እንዳልተገኘለት ነው የሚነገረው።
ሆኖም ግን የSR-71 “ብላክ በርድ” የፍጥነት ክብረወሰን በቅርቡ በተከታዩ SR-72 “ሰን ኦፍ ብላክ በርድ” አውሮፕላን ሊሰበር እንደሆነም ነው የተሰማው።
አዲሱ SR-72 “ሰን ኦፍ ብላክ በርድ” አውሮፕላን ሃይበርሶኒክ ነው የተባለ ሲሆን፤ በከፍተኛ ፍጥነት ጥቃት የሚፈጽም የሎክሄድ ማርቲን ሚስጥራዊ የጦር ጄት ነው።
ሆኖም ግን ለቅኝት፣ ለስለላ እና ልዩ ተልእኮዎችን ለመፈጸም ጥቅም ላይ እንደሚውልም ነው የተገለጸው።
እንደ ሎክሄድ ማርቲን መረጃ ከሆነ አዲሱ SR-72 “ሰን ኦፍ ብላክ በርድ” አውሮፕላን በፈረንጆቹ 2025 የመጀመሪያ በረራውን የሚያደርግ ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2030 ደግሞ ወደ አገልግሎት ይገባል።