ግብጽና ቱርክ ለአስር አመታት ሻክሮ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እያደሱ ነው
ቱርክ ታዋቂና ዘመናዊ ድሮኖቿን ለግብጽ ለመሸጥ መስማማቷን አስታወቀች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ሀበር ከተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ አንካራ ለካይሮ ድሮኖችን እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ መወሰኗን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን የካቲት ወር አጋማሽ ላይ ወደ ግብጽ እንደሚያመሩም ነው የተናገሩት።
ኤርዶሃን ከግብጽ አቻቸው አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በደህንነትና ሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ብለዋል ሚኒስትሩ።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለካይሮ የሚቀርበው የድሮን አይነት የትኛው መሆኑን በዝርዝር አልጠቀሱም።
የጦርነት አውድ ቀያሪ ናቸው የሚባልላቸው የቱርክ ድሮኖች ከሶሪያ እስከ ሊቢያ፤ ከአዘርባጃን እስከ ዩክሬን ጥቅም ላይ ውለው አለማቀፍ ተቀባይነታቸው ጨምሯል።
የህዳሴው ግድብ መገንባት ከተጀመረ አንስቶ ከግብጽ እና ሱዳን ተቃውሞ ሲቀርብባት የቆየችው ኢትዮጵያም የቱርክ ድሮኖችን መግዛቷን ሬውተርስ አስታውሷል።
በኢስታንቡል የሚገኘው “ባይካር” ኩባንያ የሚያመርታቸው “ባይካታር” ድሮኖች ተፈላጊነት እየጨመረ አንካራን በድሮን ቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅ እንዳደረጋት ተነግሯል።
ከ2013 ጀምሮ ከቱርክ ጋር ግንኙነቷ ሻክሮ የቆየው ግብጽም ጦሯን የሚያጠናክሩ ድሮኖች ታገኛለች ነው የተባለው።
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን የቀድሞው የግብጽ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልፈታህ አልሲሲ ሞሀመድ ሙርሲን በሃይል በመገልበጥ ስልጣን መያዛቸውን አጥብቀው መቃወማቸው ይታወሳል።
ይህም ካይሮን አስቆጥቶ የቃላት ልውውጡ አምባሳደሮችን እስከማስወጣት መድረሱ አይዘነጋም።
የሀገራቱ መሪዎች በኳታር ላይ የአራትዮሽ እቀባ ሲደረግ፣ በሊቢያ እና ሶሪያ ጦርነቶች ያንጸባርቋቸው አቋሞችም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ይበልጥ እያሻከረው ሄዶ ነበር።
ኳታር በ2022 የአለም ዋንጫን ስታስተናግድ ኤርዶሃን እና አልሲሲ በዶሃ እንዲገናኙ ያደረገችበት “የእግርኳስ ዲፕሎማሲ” ካይሮ እና አንካራ ለአስር አመታት የዘለቀ ውጥረታቸውን እንዲያረግቡ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
በዚህም ባለፈው አመት አምባሳደሮቻቸውን ዳግም ሾመው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማጠናከር መጀመራቸውን የሚድል ኢስት ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።