ቱርክ በአቪየሽን ተቋሟት ላይ ለደረሰው ጥቃት በሶሪያና ኢራቅ የአጻፋ እርምጃ ወሰደች
አንካራ በሽብርተኝነት የፈረጀችው የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) ይዞታዎች ላይ ነው ድብደባ የፈጸመችው
በትናንትናው እለት በተፈጸመው የሽብር ጥቃት በጥቂቱ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉና ከ22 በላይ መቁሰላቸው ተገልጿል
ቱርክ በአንካራ አቅራቢያ በትናንትናው እለት ለተፈጸመባት የሽብር ጥቃት የአጻፋ እርምጃ መውሰዷን አስታወቀች።
በጦር መሳሪያ ማምረቻው የቱርክ ኤሮስፔስ ኢንዱስትሪ (ቲዩኤስኤኤስ) ዋና መስሪያ ቤት ላይ የታጠቁ ሃይሎች በከፈቱት ተኩስ እና የቦምብ ጥቃት አምስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉና 22 ሰሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል።
ለዚህ ጥቃት እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም የቱርክ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር አሊ ይርሊካያ ግን ጥቃት አድራሾቹ የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ(ፒኬኬ) አባላት ሳይሆኑ እንደማይቀሩ በርካታ አማላካች ነገሮች እንዳሉ ተናግረዋል።
“የጥቃቱ አፈጻጸም የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ ከዚህ ጥቃት ጀርባ እንዳለ አመላካች ነው፤ የማጣራት ስራው ቀጥሏል፤ እንደተጠናቀቀ ተጨማሪ መረጃ እናቀርባለን” ማለታቸውንም ቲአርቲ ዘግቧል።
የቱርክ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ አንካራ ለትናንቱ ጥቃት የአጻፋ እርምጃ መውሰዷን አመላክቷል።
በሶሪያ እና ኢራቅ በሚገኙ 32 የፒኬኬ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙንም ነው ያስታወቀው።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አጋር እና የቀኝ ዘመሙ ናሽናሊስት ሙቭመንት ፓርቲ መሪው ዴቭሌት ባንሴሊ ከኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ ጋር ለአመታት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ምክረሃሳብ ባቀረቡ ማግስት ነው የትናንቱ የሽብር ጥቃት የተፈጸመው።
ምክረሃሳቡ በእስር ላይ የሚገኘው የፒኬኬ መሪው አብዱላህ ኦካላን በቱርክ ፓርላማ በመገኘት ታጣቂ ሃይሉ ትጥቅ እንዲፈታና ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን ንግግር እንዲያደርግ የሚጠይቅ ነው። በምትኩም መሪው ከእስር እንዲለቀቅ ይጠይቃል።
የአምስት ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የትናንቱ ጥቃት እና ይህን ተከትሎ አንካር የወሰደችው የአጻፋ እርምጃ ግን የፒኬኬ እና የቱርክ መንግስትን የአመታት ፍጥጫ የሚያስቀጥል ይመስላል።
ነጻ ኩርድን የመመስረት ግብ ያለው ፒኬኬ መስራቹ ኦክላን ከቱርክ መንግስት ጋር ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ የሰላም ድርድር ቢያደርግም ስምምነት ሳይደረስ ቀርቶ በ2015 ደም አፋሳሽ ጦርነት መካሄዱ የሚታወስ ነው።
ቱርክ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ፒኬኬን በሽብርተኝነት ድርጅት መፈረጃቸው ይታወቃል።