ቱርክ፤ በኢራቅ እና ሶሪያ ወደ 500 የሚጠጉ የኩርድ ኢላማዎችን መትቻለሁ አለች
የቱርክ እርምጃ ለኢስታምቡሉ የቦምብ ጥቃት የሚወሰድ የአጸፋ ምላሽ ነው ተብሏል
የቱርክ ፕሬዝዳንት “በቱርክ ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ ሰዎች ዋጋ ይከፍላሉ” ሲሉ መዛታቸው አይዘነጋም
ቱርክ፤ በጀመረችው አየር ጥቃት በኢራቅ እና ሶሪያ ወደ 500 የሚጠጉ የኩርድ ኢላማዎችን መምታቷን የቱርክ መከላከያ ሚንስትር ሁሉሲ አካር ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ "እስካሁን 471 ኢላማዎች ተመትተዋል እና 254 አሸባሪዎች በዘመቻው ከጥቅም ውጪ ሆነዋል" ሲሉ መናገራቸውም አናዶሉ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ማክሰኞ እለት በሶሪያ ምድር ላይ እየተካሄደ ባለው ዘመቻ ዘመቻ “ታንክም ጭምር ያለበት ወታደራዊ ዘመቻ ” እንደሚጀምሩ መዛታቸው አይዘነጋም።
“በቱርክ ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ ሰዎች ዋጋ ይከፍላሉ” ሲሉም ነበር ያስጠነቀቁት ፕሬዝዳንቱ፡፡
ቱርክ የአየር ጥቃት የጀመረችው ህዳር 13 በኢስታንቡል በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት 6 ሰዎች መሞታቸው እና 81 መቁሰላቸው ተከትሎ ነበር፡፡
የቱርክ መንግስት ለጥቃቱ ህገ-ወጥ የኩርዲስታን የሰራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) ተጠያቂ ማድረጉም የሚታወስ ነው፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የቦምብ ፍንዳታውን “የሽብር ጠረን” ያለበት “መጥፎ ጥቃት” ሲሉም ነበር የጠሩት በወቅቱ።
እናም የአሁኑ የቱርክ የአየር ላይ ጥቃት ቱርክ በኩርድ ታጣቂዎች ላይ የምትወስደው የአጸፋ እርምጃ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
የአንካራ ሰዎች የተሳካ ወታደራ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ቢሆኑም፤ ነገሩ በሩሲያ በኩል የተወደደ አይመስልም፡፡
ሩሲያ ቱርክ በሶሪያ ውስጥ "ከልክ በላይ" ወታደራዊ ኃይልን ባለመጠቀም ውጥረቱ እንዳይባባስ በማድረግ በኩል ጥንቃቄ ታድግ ስትል በትናንትናው እለት ባወጣችው መግለጫ ጠይቃለች፡፡
የሩሲያ የዜና ኤጀንሲዎች እንደዘገቡት ከሆነ በሶሪያ የሩስያ መልዕከተኛ አሌክሳንደር ላቭሬንትዬቭ "በሶሪያ ሰሜናዊ እና ሰሜናዊ ምስራቅ ክልሎች ብቻ ሳይሆን በመላው ግዛቱ ውስጥ ያለው ውጥረት እንዳይባባስ ለመከላከል የቱርክ ባልደረቦቻችን የተወሰነ ገደብ እንዲያሳዩ እንጠይቃለን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ላቭሬንትዬቭ "የቱርክ አጋሮቻችን በሶሪያ ግዛት ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ለማሳመን ተስፋ እናደርጋለን"ም ብለዋል፡፡
አክለውም ሩሲያ ፍላጎት ካላቸው አካላት ጋር "የኩርድ ጉዳይ" ላይ ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ እንደምትሰራ ገልጸዋል።