በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ አቅራቢያ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት የሰዎች ህይወት አለፈ
ጥቃቱ የጦር አውሮፕላኖችን በሚያመርት የአቭየሽን ተቋም ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ተሰምቷል
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በጥቃቱ የደረሰ ከፍተኛ ፍንዳታን አሳይተዋል
በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ አቅራቢያ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት በሰዎች እና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተነገረ፡፡
ጥቃቱ ከአንካራ 40 ኪሎሜትር አቅራቢያ ላይ በሚገኘው የቱርክ ኤሮስፔስ ኢንደስትሪ (በቱኤስኤስ) ዋና መሥሪያ ቤት ያነጣጠረ ነው ተብሏል፡፡
የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን በቦታው ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ እንደደረሰ እና የተኩስ ልውውጥን የሚያሳይ ምስል አጋርተዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ይርሊካያ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ “በ አንካራ አቅራቢያ ካህራማንካዛን ውስጥ በቱኤስኤስ ተቋም ላይ የሽብር ጥቃት ተፈጽሟል፤ እንደ አለመታደል ሆኖ በጥቃቱ የሞቱ እና የተጎዱ ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጠናል” ብለዋል።
የተኩስ ልውውጡ እና የፍንዳታው መንስኤ እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን አንዳንድ ሚዲያዎች የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ተፈጽሟል ሲሉ ዘግበዋል።
በአሁኑ ወቅትም አምቡላንስ ፣ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እና የጸጥታ ሀይሎችን ያካተተ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ቡድን ወደ ቦታው መላኩን ሮይተርስ የቱርክ ዜና ኤጄንሲ አናዶሉን ጠቅሶ አስነብቧል።
የቴሌቪዥን ምስሎች በፍንዳታው የአቭየሽን ተቋሙ በር መጎዳቱን እንዲሁም በመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች አቅራቢያ በጸጥታ ሀይሎች እና ጥቃቱን ፈጽመዋል በተባሉ አካላት መካከል የተኩስ ልውውጦችን አሳይተዋል፡፡
የተጎጂዎችን ቁጥር በይፋ ያልገለጹት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ስለሁኔታው ዝርዝር መረጃዎችን በይፋ እንደሚገለጽ ቃል ገብተው ህብረተሰቡ የመንግስት ይፋዊ መግለጫዎችን በትዕግስት እንዲጠባበቅ አሳስበዋል፡፡
ቱኤስኤስ ከቱርክ አስፈላጊ የመከላከያ እና አቪዬሽን ኩባንያዎች መካከል አንዱ ሲሆን በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን “ካን” የጦር አውሮፕላንን ጨምሮ ሌሎች የውጊያ አውሮፕላኖችን ያመርታል፡፡