ክርስቲያን አትሱ በቱርክ በሚገኝ ቤቱ ሞቶ ተገኘ
የቱርኩ ክለብ ሃታይስፖር አትሱ ከርዕደ መሬት አደጋው መትረፉን ገልጾ የነበረ ሲሆን፥ ከአደጋው ከ12 ቀናት በኋላ ሞቶ መገኘቱ ተገልጿል
ጋናዊው የ31 አመት ተጫዋች በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለቼልሲ እና ኒውካስትል መጫወቱ ይታወሳል
የቀድሞው የቼልሲ እና ኒውካስትል ተጫዋች ክርስቲያን አትሱ በቱርክ በሚገኘው ቤቱ ውስጥ ህይወቱ አልፎ መገኘቱ ተነገረ።
ወኪሉ ናና ሰቸሬ ከስአታት በፊት በትዊተር ገፁ እንዳሰፈረው፥ አትሱ በርዕደ መሬቱ ከፈራረሰ ቤቱ ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል።
ክለቡ ሃታይስፖር ክርስቲያን አትሱ በሃታይ ከተማ ከሚገኝ ቤቱ ከፍርስራሽ ውስጥ ህይወቱ ሳያልፍ መገኘቱን ከ10 ቀናት በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።
ይህንኑ ዜና መገናኛ ብዙሃን ከተቀባበሉት ከአንድ ቀን በኋላም ክለቡ ጉዳት ደርሶበት ተርፏል የሚለው ዜና ሀሰት መሆኑን መግለፁን ቢቢሲ አስታውሷል።
አሰቃቂው ርዕደ መሬት ከደረሰ ሁለት ሳምንቱን ሊይዝ ሲቃረብም ዛሬ ጠዋት የአትሱ አስከሬን ከፍርስራሽ ውስጥ መውጣቱን ወኪሉ ናና ሰቸሬ ገልጿል።
ለቤተሰቦቹና ለአደናቂዎቹ መፅናናትን የተመኘው ሰቸሬ፥ ለአትሱ ሲፀልዩ ለቆዩትም ምስጋናውን አቅርቧል።
የተጫዋቹ ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ለምርመራ መላካቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በመኖሪያ ቤቱ ሌላ ሰው ሞቶ ስለመገኘቱ አልተጠቀሰም።
ኒውካስትልን ጨምሮ የአትሱ አድናቂ ስፓርተኞች ጋናዊው ተጫዋች ከአደጋው ይተርፍ ዘንድ ሲመኙለት መቆየታቸው ይታወሳል።
የቱርክን 10 ግዛቶች ክፉኛ የጎዳው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እስካሁን 40 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል።
በሶሪያም ከ5 ሺህ 800 በላይ ሰዎችን የገደለው አደጋ ሚሊየኖችን አፈናቅሏል።