“አያ” - እትብቷ ሳይበጠስ ፍርስራሽ ውስጥ የተገኘችው ሕጻን
በአረብኛ “የፈጣሪ ምልክት” የሚል ትርጓሜ ያለው ስም የተሰጣት ህጻን በሶሪያ በደረሰው ርዕደ መሬት ወቅት ተወልዳ እናቷ ህይወቷ ሲያልፍ በተአምር ተርፋለች
አደጋው ከደረሰ ከ10 ስአት በኋላ ፍርስራሽ ውስጥ የተገኘችው ህጻን አሁን በጥሩ ጤንነት ላይ ትገኛለች ተብሏል
በሶሪያና በቱርክ ከደረሰው አሰቃቂ ርዕደ መሬት ከተረፉ ሰዎች ውስጥ የሰሜን ሶሪያዋ “አያ” አስደናቂ ሆኖ መገናኛ ብዙሃን ተቀባብለውታል።
አያ በዚያ በጭንቅ ጊዜ ነው ይህቺን አለም በለቅሶ የተቀላቀለችው።
- በቱርክ የርዕደ መሬት አደጋ በፍርስራሽ ተቀብራ የነበረች ሴት ከ3 ቀናት በኋላ በህይወት ተገኘች
- የቱርክ እና ሶሪያን ርዕደ መሬት የተነበየው ሆላንዳዊ ቀጣይ ተረኞቹ እነማን ናቸው አለ?
እናቷ አፍራ አቡ ሃዲያ በምጥ ላይ በነበረችበት ወቅት ርዕደ መሬቱ የመኖሪያ ህንጻቸውን ወደ ፍርስራሽነት ለውጦታል።
ይሁን እንጂ አፍራ ከርዕደ መሬቱ ጋር እየታገለችም ቢሆን ለነገ የማይሉትን ምጥ አምጣ ልጇን ተገላግላለች።
ከአጠገቧ አይዞሽ የሚሏትን በአደጋው ምክንያት ያጣችው አፍራም ህይወት ሰጥታ ወደማይቀረው አለም ስትሰናበት ግን ጊዜ አልወሰደባትም።
“አያ” እትብቷ ሳይቆረጥ አዲስ በሆነው አለም ብቻዋን ፍርስራሽ ውስጥ ለመቆየትም ተገዳለች።
ርዕደ መሬቱ ከደረሰ ከ10 ስአት በኋላ ግን ትረፊ ያላት ነፍስ እንዲሉ የነፍስ አድን ሰራተኞች እትብቷን ቆርጠው ከፍርስራሽ አወጧት ይላል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
በአረብኛ “የፈጣሪ ምልክት” የሚል ትርጓሜ ያለው ስም ተሰጥቷትም ወደ ሆስፒታል ተወስዳለች።
ባለፉት ቀናት በተደረገላት ህክምናም ጤናዋ መስተካከሉ በመረጋገጡ ዛሬ ወይም ነገ ከሆስፒታል ትወጣለች ተብሏል።
ሳሌህ አል ባድራን የተባለች አክስቷም ልታሳድጋት ቃል መግባቷን ዘገባው አክሏል።
አያ በርዕደ መሬቱ አምጣ የወለደቻት እናቷ ብቻ አይደለችም የሞተችባት፤ አባቱ እና አራት ወንድምና እህቶቿም በአደጋው ህይወታቸው አልፏል።
ከቤተሰቡ በአሰደናቂ ተአምር የተረፈችው “የፈጣሪ ምልክቷ”፥ ከ5 ሺህ በላይ ሶሪያውያንን የጨረሰውን አደጋ አሸንፋ የነገ ተስፋ ሆናለች።
በሰሜናዊ ሶሪያ አፍሪን ከተማ በሚገኘው ሲሃን ሆስፒታል ሲሰጣት የቆየውን መድሃኒት አቁማም የሆስፒታሉን ሜዲካል ዳይሬክተር ሚስት ጡት እየጠባች ነው።
የአያ ቤተሰቦች በምስራቃዊ ሶሪያ ዴር ኤል ዙር ግዛት ክህሻም በተባለ መንደር ነበር የሚኖሩት።
ከፈረንጆቹ 2018 ወዲህ ግን የአይ ኤስ የሽብር ቡድንን ሸሽተው በሰሜን ሶሪያ አፍሪካ አካባቢ ጂንደሪስ በተባለች መንደር መኖር መጀመራቸውን ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ። ሽብርን ቢሸሹም የተፈጥሮ አደጋውን ግን ማምለጥ አልቻሉም።