ቱርክ የስዊድንን የኔቶ አባልነት አጸደቀች
አንካራ ከ20 ወራት በኋላ ስቶኮልም ወደ ኔቶ እንድትቀላቀል በመፍቀዷ ከአሜሪካ ኤፍ- 16 የጦር አውሮፕላኖችን መግዛት ይፈቀድላታል ተብሏል
ስዊድን 32ኛዋ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት አባል ለመሆን የሀንጋሪን ይሁንታ ትጠብቃለች
የቱርክ ፓርላማ የስዊድንን የኔቶ አባልነት ጥያቄ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።
የፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ፓርቲ ኤኬ አብላጫ በያዘበት ፓርላማ ለ20 ወራት ሲንከባለል የቆየው ጥያቄ 287 ለ55 በሆነ ድምጽ ጸድቋል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት አባል ለመሆን ጥያቄ የሚያቀርቡ ሀገራት በሁሉም አባል ሀገራት ድጋፍ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
ሩሲያ በዩክሬን የከፈተችው ጦርነት አሳስቦናል ያሉት ፊንላንድ እና ስዊድን በ2022 ኔቶን ለመቀላቀል ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ቱርክ እና ሀንጋሪ ለሀገራቱ ጥያቄ ድጋፍ ለመስጠት አመንትተው በመቆየት የፊንላንድ ጥያቄ ባለፈው አመት ተቀባይነት ማግኘቱ አይዘነጋም።
በስዊድን የተደረጉ የቅዱስ ቁርአን ማቃጠል ተግባራት ያስቆጣት አንካራ ለስቶኮልም ጥያቄ ምላሽ ሳትሰጥ ብትቆይም በትናንትናው እለት በፓርላማዋ አጽድቃዋለች።
የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቶቢያስ ቢልስትሮም የቱርክ ፓርላማ ያሳለፈውን ውሳኔ አድንቀዋል።
የኔቶ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግም የአንካራን ውሳኔ አድንቀው ሀንጋሪም ተመሳሳይ አቋም እንድትይዝ ጠይቀዋል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ፓርላማው ያጸደቀው ሰነድ ላይ እንደሚፈርሙ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ስዊድን 32ኛዋ የኔቶ አባል ሀገር ለመሆን የሚቀራት የሀንጋሪ ይሁንታ ይሆናል።
ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸውና የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን የ60 ቢሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ እንዳያጸድቅ የተቃወሙት የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን የስዊድን አቻቸውን ለድርድር ጋብዘዋል።
ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ቱርክ እና ሀንጋሪ የፊንላንድ እና የስዊድንን የኔቶ አባልነት ማጽደቅ የድርጅቱ መስፋፋት የህልውና ስጋቴ ነው ያለችውን ሞስኮ ማስቆጣቱ አይቀሬ ነው።
አንካራ ግን የስቶኮልምን ጥያቄ ስትቀበል ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎቿ ተፈተውላት ጥቅሟን አስከብራበታለች ነው የተባለው።
ስዊድን በሀገሪቱ የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) አባል መሆንን የሚከለክል የጸረ ሽብር ህግ አውጥታለች፤ ቅዱስ ቁርአንን በሚያቃጥሉ አካላት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ለመውሰድም ቃል ገብታለች።
በጥቅምት ወር የስዊድንን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ወደ ፓርላማቸው የላኩት ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን፥ የስቶኮልምን ጥያቄ ለማጽደቅ አሜሪካ ኤፍ - 16 ተዋጊ ጄቶችን ልትሸጥልን ይገባል ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ዋይትሃውስ ሽያጩን የደገፈ ሲሆን በቀጣይ ኮንግረንሱ ተወያይቶ እንደሚያጸድቀውም ይጠበቃል።