ተመድ የቱርክን አዲስ ስያሜ ማጽደቁን ገልጿል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቱርክ ስሟ እንዲቀየር ያቀረበችለትን ጥያቄ ማጽደቁን አስታወቀ፡፡
ቱርክ መጠሪያዋን ቱርኪ እንዲባል ፍላጎት አሳድራ የነበረው ከታህሳስ ጀምሮ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ቱርክ ስሟ እንዲቀየርላት ያቀረበችውን ጥያቄ ተከትሎ ነው ተመድ ቅያሬውን ያጸደቀው፡፡
የካምብሪጅ መዝገበ ቃላት ቱርክ የሚለውን በመጥፎ ሁኔታ መውደቅ፣ ወይም የማይረባና የማይጠቅም ሰው በሚል ይተረጉመዋል፡፡
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጠይብ ኤርዶሃን ቱርኪዬ (ተርኪዬ) የሚለው መጠሪያ የሀገሪቱን ህዝብ ስልጣኔ ፣ባህል እና እሴት በዋናነት የሚገልጽ እና የሚወክል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ሀገራትና ተቋማት አዲሱን ስም እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሀገሪቱ ተመርተው ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችም ``በተርኪዬ የተመረተ`` የሚል ጹሑፍ እንዲኖርባቸው ታዟል፡፡ የቱርክ ዜጎች በአዲስ መልክ የቀረበውን መጠሪያ ቀደም ሲል ይጠቀሙት ነበርም ተብሏል፡፡
የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ቱርክ ስሟ እንዲቀየርላት የተዘጋጀውን ደብዳቤ ለተመድ ማስረከባቸው ተሰምቷል፡፡
የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፈን ጁጃሪችም ትናንትና ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተላከ ደብዳቤ ለዋና ጸሐፊ አንቲኒዮ ጉቴሬዝ መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡
አዲሱ የቱርክ ስያሜ ደብዳቤው ገቢ ከሆነበት ዕለት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡ ሀገሪቱ የሥም ለውጥ በማድረግ ለዓለም ራሷን በአዲስ መልክ ለማሳየት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ተገልጿል፡፡
የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ይህንን የሥም ለውጥ በተመለከተ የተዘጋጀውን ደብዳቤ ማክሰኞ ዕለት ለተመድ እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲደርስ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
የስም መቀየሩን ስራ ከሀገሪቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ጋር በመሆን በጥሩ መሰረት ላይ መዘጋጀቱም በደብዳቤው ተገልጿል ተብሏል፡፡ በቱርክ ቋንቋ የሀገሪቱ መጠሪያ ቱርኪዬ ሲሆን በእንግሊዝኛ ግን መጥፎ ትርጉም እንዳለው ይጠቀሳል፡፡ ከምዕራባውያን አገዛዝ በ 1923 ነጻ ወጣችው ቱርክ በምዕራባውያን ኦቶማን ስቴት ወይም ቱርኪዬ እየተባለች ትጠራ ነበር፡፡
በ 2018 ስዋዚላንድ ስሟን ወደ እስዋቲኒ መቀየሯ የሚታወስ ሲሆን እ.ኤ.አ ከ 1935 በፊት ኢራንም ፐርሺያ ተብላ ትጠራ ነበር፡፡ ሜቄዶኒያ ከግሪክ ጋር ባላት ውዝግብ ምክንያት ስያሜዋን ወደ ሰሜን ሜቄዶኒያ ስትቀይር፤ ታይላንድ ሲያም፤ ዜምባብዌ ደግሞ ሮዴሻ በመባል ይጠሩ ነበር፡፡