ብሪታኒያ፤ ቱርክ ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን መቀላቀላቸውን እንድትቀበል እያግባባች ነው ተባለ
ቱርክ፤ ፊንላንድ እና ስዊድን የኔቶ አባል መሆናቸውን መቃወሟ ይታወሳል
ጠ/ሚ ቦሪስ ጆንሰን የቱርክ ፕሬዝዳንትን ኤርዶሃንን እያግባቡ መሆኑ ተገልጿል
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ስዊድን እና ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል እንዲሆኑ የቱርኩን ፕሬዝዳንት እያግባቡ መሆኑ ነው ተባለ፡፡
ከሰሞኑ የኔቶ አባል ለመሆን ጥያቄ ያቀረቡት ስዊድን እና ፊንላንድ ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣኢብ ኤርዶሃን ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎም ነው ቦሪስ ጆንሰን ፤ የቱርኩን ፕሬዝዳንት እያግባቡ ያሉት፡፡
ጆንሰን፤ ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን ቢቀላቀሉ ተጨማሪ እሴት ሊሆኑ እንደሚችሉ ለረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ነግረዋቸዋል ተብሏል፡፡
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ እንዳስታወቀው፤ ቦሪስ ጆንሰን በስዊድንና ፊንላንድ ጉዳይ ከኤርዶሃን ጋር ለመስራት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሰረት ቱርክ፣ ስዊድንና ፊንላንድ እንዲሁም ኔቶ በጋራ እንዲሰሩ ብሪታኒያ ፍላጎት አላት፡፡ ብሪታኒያ በቀጣይ ወር በስፔን ማድሪድ በሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ላይ ሁሉም ወገኖች አብረው እንዲሰሩ ትደግፋለች ተብሏል፡፡
ጆንሰን እና ኤርዶሃን የዩክሬናውያንን ስቃይ ለመቀነስ የሚስችል የእህል መተላለፊያ እንዳይዘጋም ተነጋግረዋል ተብሏል፡፡
ፊንላንድ እና ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ለመቀላቀል መወሰናቸውን ተከትሎ ሩሲያ የአፀፋ እርምጃ መውሰድ መጀመሯን ገልጻለች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጊ ሾይጉ በሰጡት አስተያየት፤ ፊንላንድ እና ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ለመቀላቀል መወሰናቸው በሩሲያ ድንበር አካባቢ ወታደራዊ ስጋቶች እንዲጨምሩ ያደርጋል ብለዋል።