በቱርክ እና ሶሪያ ባጋጠመው ርዕደ መሬት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 20 ሺህ መድረሱ ተገለጸ
በቱርክ ብቻ 17 ሺህ 600 ሰዎች መሞታቸው መረጃዎች ያመለክታሉ
የተመድ ዋና ጸሃፊው ፤ የአደጋው መጠን እጅግ ከባድ መሆኑ "አሁን እየተገለጠልን ነው " ሲሉ አስጠንቅቀዋል
ሰኞ እለት ቱርክ እና ሶሪያን በመታው ርዕደ መሬት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 20 ሺህ መድረሱ ተገለጸ፡፡
100 ሺህ ያህሉ የነፍስ አድን ሰራተኞች አሁንም ድረስ የሰዎችን ህይወት ለማታደግ የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ላይ ቢሆኑም ካለው ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ ጋር ተዳምሮ ነገሮች ከባድ እየሆኑ መጥተዋል፡፡፡
በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ውሃና ምግብ ሳያገኙ ለችግር መዳረጋቸው የሚያመለክቱ ዘገባዎች እየወጡ ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደጋው መጠንና ያስከተለው ጉዳት በግልጽ ለማወቅ አለመቻሉ ሁኔታው አሳሳቢ አድርጎታል ብሏል።
በተለይም በጦርነት ስትታመስ በቆየችው ሶሪያ ላይ ያለው የአደጋ መጠን ማወቅ አለመቻሉ ተመድ ገልጿል፡፡
የተመድ ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የአደጋው መጠን እጅግ ከባድ መሆኑ "አሁን እየተገለጠልን ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
አሁን ላይ ከቱርክ ወደ ሰሜን ምእራብ ሶሪያ ሰብዓዊ ርዳታ መላክ መጀመሩን የገለጹት ዋና ጸሃፊው፤ ድጋፉ በሌሎች መስመሮችም ጭምር እንዲገባ የጸጥታው ምክር ቤት ኃላፊነቱ እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
"አሁን አንድነት የሚያስፈልግብት ወቅት ላይ ነው ያለነው፤ ፖለቲካ የሚሰራበት ጊዜ አይደለም ፤ ሰፊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግን ግልጽ ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሮይቶርስ የቱርክ ባለስልጣናት መረጃን ጠቅሶ እንደዘገበው ርዕደ መሬቱን ተከትሎ እስካሁን 17 ሺህ 600 ሰዎች ሞተዋል፡፡
በሶሪያም እንዲሁ 3ሺህ 377 ያህሉ ሰዎች ህይወታቸው አልፈዋል፡፡
በሬክተር ስኬል 7.8 የተመሰገበው የአሁኑ አደጋ እንደፈረንጆቹ 1999 በሰሜን ምዕራብ ቱርክ ካጋጠመውና የ17 ሺህ ሰዎች ህይወት ከቀጠፈው አደጋ የከፋ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዳን በበኩላቸው በሀገሪቱ የደረሰውን ርዕደ መሬት " የክፍለ ዘመኑ አስከፊ አደጋ " ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡
አሁን ላይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቱርካውያን እና ሶሪያውያን በግዜያዊ መጠለያ ጣቢያች ከሰፈሩ አራት ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ካለው የአየር ሁኔታ ጠባይ አንጻር ለከፍተኛ ቅዝቃዜ ተጋልጠውም ይገኛሉ፡፡