ክርስቲያን አትሱ ከቱርክ ርዕደ መሬት ተርፎ ከፍርስራሽ ወጣ
የቀድሞው የቼልሲ እና ኒውካስትል ተጫዋች መጠነኛ ጉዳት ቢደርስበትም ከብዙ ድካም በኋላ ከፍርስራሽ እንዲወጣ ተደርጓል
የሃትሱ ክለብ ሃታይስፐር ስፖርቲንግ ዳይሬክተሩ ታነር ሳቩት ግን አሁንም በፈረሰ ህንጻ ውስጥ ነው ተብሏል
የቀድሞው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የፊት መስመር ተጫዋች ክርሲያን አትሱ ከቱርኩ ርዕደ መሬት በተአምር ከተረፉት መካከል አንዱ ሆኗል።
የቀድሞው የቼልሲ እና ኒውካስትል አጥቂ፥ ለሶሪያ ድንበር ቅርብ በሆነችው የቱርኳ ሃታይ ግዛት እያለ ነው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው የተከሰተው።
ለቱርኩ ሃታይስፖር የሚጫወተው ክርስቲያን አትሱ፥ የትናንቱ ርዕደ መሬት የነበረበትን ህንጻ በላዩ ላይ አፈራርሶበት መውጣት ተስኖት መቆየቱን ወኪሉ ሙስጠፋ ኦዛት ለቱርኩ ቻናል ራዲዮ ጎል ተናግሯል።
ለስአታት ከተካሄደ የነፍስ አድን ስራ በኋላም ጋናዊውን ተጫዋች ከፍርስራሽ ውስጥ ማውጣት መቻሉንም ነው ያነሳው።
ክርስቲያን አትሱ በፍርስራሽ ውስጥ መቀበሩ እንደተሰማ ኒውካስትልን ጨምሮ የተለያዩ ክለቦች በሰላም ይወጣ ዘንድ ምኞታቸውን ገልጸውለታል።
የ31 አመቱ ተጫዋች ጉዳት ቢያስተናግድም በነፍስ አድን ሰራተኞች ከፍርስራሽ ውስጥ እንዲወጣ መደረጉም ለበርካቶች ተስፋን መስጠቱን የብሪታንያው አይ ኒውስ አስነብቧል።
የሃታይስፖር ክለብ ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ታነር ሳቩት ግን አሁንም በፍርስራሽ ውስጥ ነው ተብሏል።
የመጨረሻዎቹ የነፍስ አድን ሙከራዎች መልካም ዜናን ይዘው እንዲመጡም ሙስጠፋ ኦዛት ምኞቱን ገልጿል።
የቱርክን 10 ግዛቶች ክፉኛ የጎዳው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፤ ከ20 በላይ ሰዎችም መቁሰላቸው ነው የተነገረው።
ክርስቲያን አትሱ ጉዳት ያስተናገደባት ሃታይ ግዛትም በርዕደ መሬቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ህንጻዎቿ ፈራርሰውባታል።
ቱርክ ከ9 ሺህ በላይ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን አሰማርታ የነፍስ አድንስራው መቀጠሉ እየተነገረ ነው።
ብሪታንያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትም አስቸኳይ ድጋፍን ለማድረግ ባለሙያዎችን መላካቸው ተሰምቷል።