አሜሪካ ወደ ቱርክ የነፍስ አድን ስራተኞችና ውሻዎች ላከች
የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤይድ 160 የነፍስ አድን ሰራተኞች እና 12 የሰለጠኑ ውሻዎችን ዛሬ በአዲያማን ግዛት ያሰማራል ተብሏል
ከ6 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ርዕደ መሬት የነፍስ አድን ስራ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል
በቱርክ በደረሰው አሰቃቂ ርዕደ መሬት አሁንም ድረስ በፍርስራሽ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ህይወት የማትረፍ ርብርቡ ቀጥሏል።
ሶስተኛ ቀኑን በያዘው የነፍስ አድን ስራ ህጻናት እና ነፍሰጡሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን ማዳን መቻሉንም ከቱርክ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች ያመላክታሉ።
ከ9 ሺህ በላይ የነፍስ አድን ሰራተኞችን ያሰማራችው አንካራ፥ ወዳጅ ሀገራትና ተቋማት በፍጥነት እንዲደርሱላት ጥሪ ማቅረቧም የሚታወስ ነው።
አሜሪካም በዛሬው እለት በአዲያማን ግዛት በዚሁ የነፍስ አድን ተልዕኮ ውስጥ እንደምትሰማራ አስታውቃለች።
የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት በሁለት ቡድኖች 160 የአደጋ ሰራተኞችን እና 12 አነፍናፊ ውሻዎችን በማሰማራት የበርካቶችን ህይወት ለመታደግ እንደሚሰራ ነው ይፋ ያደረግው።
ሰዎች ላይ የወደቁ የህንጻ ፍርስራሾችን የሚያነሱ መሳሪያዎችም ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ነው የዩኤስኤይድ የርዕደ መሬት አደጋ ምላሽ አስተባባሪው ስቴፈን አለን የተናገሩት።
“እያንዳንዱ ደቂቃ የሰዎችን በህይወት የመቆየት እድሜ ስለሚወስኑም 24 ስአት የነፍስ አድን ስራውን እናከናውናለን” ሲሉም ተደምጠዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለቱርኩ አቻቸው ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ደውለው ዋሽንግተን በዚህ ፈታኝ ወቅት ከአንካራ ጎን እንደምትቆም ማረጋገጣቸውን ቲ አር ቲ ወርልድ አስነብቧል።
ከአሜሪካ ባሻገርም የቱርክ ጎረቤት ሀገራት በነፍስ ማዳን ስራውና አስቸኳይ ድጋፎችን በመላክ አጋርነታቸውን እያሳዩ መሆኑም ተገልጿል።
በተመሳሳይ ርዕደ መሬት ተመታ ከ2 ሺህ በላይ ዜጎቿ የሞቱባት ሶሪያ ግን ተገቢውን ትኩረት አላገኘችም።የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት ግን ለሶሪያም ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ከለጋሽ ተቋማት ጋር እየተነጋገርኩ ነው ብሏል።