ቱርክ ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት “ሙሉ በሙሉ አቋርጫለሁ” አለች
በቱርክና እስራኤል መካከል የሚደረጉ የወጪና ገቢ ንግዶች መቆማቸውን አንካራ አስታውቃለች
በ2023 ቱርክና እስራኤል መካከል የነበረው የንግድ ልውውጥ 6.8 ቢሊዮን ዶላር ነበር
ቱርክ ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጧን አስታወቀች።
ቱርክ ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ያቋረጠችው በጋዛ እየተባባሰ ከመጣው የሰብዓዉ ሁኔታ ጋር ተያይዞ እንደሆነ የሀገሪቱ ንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የቱርክ የንግድ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ ከቱርክ ወደ እስራኤል እንዲሁም ከእስራኤል ወደ ቱርክ የሚደረጉ ሁሉም አይነት የገቢና ወጪ ንግዶች ሙሉ በሙሉ ተቋርጠዋል ብሏል።
የእስራኤል መንግስት ለጋዛ በቂ እና ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲደርስ እስከሚያደርግ ድረስ ቱርክ አዲስ ያወጣችውን የንግድ ግንኙነት ማቋረጥ ውሳኔ ተግባራዊ እንደምታደርግም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ቱርክ የንግድ ግንኙነት የማቋረጥ ውሳኔውን ያሳለፈችው የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ከወደቦች ስምምነቶችን ጥሰዋል በሚል መክሰሱን ተከትሎ ነው።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትዝ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “የቱርክ ባለሃብቶችን ፍላጎት ችላ ማለት እና ዓለም አቀፍ ስምምነትን በመጣስ ወደቦችን መከልከል የአምባገነኖች ተግባር ነው” ብለዋል።
ካትዝ አክለውም ከቱርክ ጋር የነበረውን የንግድ ግንኙነቶችን ለመተካት አማራጭ እንዲፈለግ እና ከቱርክ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ላይ እንዲሰራ ለመስሪያ ቤታቸው አቅጣጫ መስጠታቸውንም አስታውቀዋል።
ቱርክ ባሳለፍነው ወር በእስራኤል ላይ የንግድ ማእቀቦችን ጥላ የነበረ ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ እስራኤል ለጋዛ ከአየር ላይ ድጋፍ እንዳልወረውር ከልክላኛለች የሚል እንደሆነም ተነግሯል።
በፈረንጆቹ 2023 ቱርክና እስራኤል መካከል የነበረው የንግድ ልውውጥ 6.8 ቢሊዮን ዶላር እንደነበረ ተነግሯል።