ቱርክ በእስራኤል ላይ የቀረበውን የዘር ማጥፋት ክስ ደግፋ ለመከራከር በይፋ ጥያቄ ለማቅረብ ወሰነች
ፊዳን አንካራ በደቡብ አፍሪካ የቀረበውን ክስ ደግፋ በአይሲጄ ለመከራከር መወሰኗን የተናገሩት በዚህ ዘር መጀመሪያ ነበር
ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ የዘርማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች በማለት በአይሲጄ እስራኤልን መክሰሷ ይታወሳል
ቱርክ በእስራኤል ላይ የቀረበውን የዘር ማጥፋት ክስ ደግፋ ለመከራከር በይፋ ጥያቄ ለማቅረብ ወሰነች።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊዳን እንደገለጹት ደቡብ አፍሪካ በአለምአቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት(አይሲጄ) በእስራኤል ላይ ያቀረበችውን የዘር ማጥፋት ክስ ደግፉ ለመከራከር ይፋዊ ጥያቄ ለማቅረብ ወሰናለች።
ፊዳን አንካራ በደቡብ አፍሪካ የቀረበውን ክስ ደግፋ በአይሲጄ ለመከራከር መወሰኗን የተናገሩት በዚህ ዘር መጀመሪያ ነበር።
እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለውን ጦርነት በጽኑ የምታወግዘው ቱርክ፣ በእስራኤል ላይ እየወሰደች ያለውን እርምጃ አጠናክራ ቀጥላለች።
ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ "ባለፈው ጥቅምት ሰባት ሀማስ በንጹሃን ላይ የፈጸመውን ግድያ እናወግዛለን" ብለዋል።
"ነገርግን እስራኤል ስልታዊ በሆነ መንገድ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ገድላለች፤ ሁሉንም የመኖሪያ መንደሮች በማውደም ሰው እንዳይኖርባቸው በማድረግ ሰብአዊ ወንጀል ፈጽማለች፤ ይህም የዘር ማጥፋት መገለጫ ነው።"
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ቱርክ በአይሲጄ ክርክር እየተደረገበት ባለው ደቡብ አፍሪካ ባቀረበችው ክስ ላይ ለመሳተፍ ይፋዊ ጥያቄ አላቀረበችም ነበር።
የቱርኩ ፕሬዜደንት ኢርዶጋንም በቱርክ በተካሄዱ ጸረ-እስራኤል የተቃውሞ ሰልፎች ላይ እስራኤል የዘርማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲሉ በአደባባይ መወንጀላቸው ይታወሳል።
ኢርዶጋን በትናንትናው እለት አሜሪካ እና አውሮፓ፣ እስራኤል ተኩስ አቁም ለማድረግ እንድትስማማ በቂ ጫና አላሳደሩባትም የሚል ወቀሳ አቅርበዋል።
በቅርቡ ሀማስ አደራዳሪዎቹ ግብጹ እና ኳታር ያቀረቡትን ሶስት ምዕራፍ ያለው የተኩስ አቁም እቅድ ተቀብሎት ነበር። ነገርግን እስራኤል የምትፈልጋቸው ቅደመ ሁኔታዎች አለመሟላታቸውን በመግለጽ እቅዱን አልተቀበለችውም።
ኢርዶጋን በኢስታንቡል በተካሄደው የሙስሊም ምሁራን ስብሰባ ላይ ሀማስ፣ ግብጽ እና ኳታር ያቀረቡትን የተኩስ አቁም እቅድ ተቀብሏል፤ ነገርግን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጦርነቱ እንዲቆም አይፈልጉም ሲሉ ተናግረዋል።
"የኔታንያሁ መንግስት ፍላጎት በራፋ የሚገኙ ንጹሀንን ማጥቃት ነው" ያሉት ኢርዶጋን "አሁን ላይ ማን ሰላም እና ንግግር እንደሚፈልግ እና ማን ቀጣይነት ያለው ግጭት እንደሚፈልግ ግልጽ ሆኗል" ብለዋል።
ሀማስ፣ እስራኤል እቁዱን ወድቅ ማድረጓን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ድርድሩ ወደ ዜሮ መመለሱን ገልጿል።