ቱርክ የስዊድንን የኔቶ አባልነት ጥያቄ የማጸድቀው የአውሮፓ ህብረት አባል እንድትሆን ከፈቀደ ብቻ ነው ስትል በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጣለች
የአውሮፓ ህብረት የቱርክን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ አደረገ።
ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ በቱርክ ምክንያት ዘግይቷል።
ከ30 በላይ በሆኑ የአውሮፓ እና አሜሪካ ሀገራት የተመሰረተው ኔቶ አዲስ አባል ሀገር ለመቀበል የግድ ሁሉም ሀገራት ፈቃደኛ መሆን አለባቸው።
የስዊድንም የኔቶ አባልነት ጥያቄ በቱርክ ምክንያት የዘገየ ሲሆን አንካራ የኩርድ ታጣቂዎች በስዊድን ተጠልለዋል የሚል ቅሬታ አላት።
ስዊድን የኩርድ ታጣቂዎችን አሳልፋ ካልሰጠችኝ ስትል የቆየችው ቱርክ አሁን ደግሞ ሌላ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጧ ተገልጿል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን እንዳሉት ኔቶ የስዊድንን የኔቶ አባልነት ጥያቄ እንድናጸድቅ ከመጠየቁ በፊት አንካራ ከ50 ዓመት በፊታ ላቀረበችው ጥያቄ ምላሽ ይስጥ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ የኔቶ እና የአውሮፓ ህብረት አባልነት ፈጽሞ የማይገናኙ ነገሮች ናቸው ሲል የፕሬዝዳንት ኤርዶሃንን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል ሲል ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ቱርክ ህብረቱን ለመቀላቀል ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት አንካራ ልታሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶች አሉ ቱርክ ከህብረቱ የአባልነት መስፈርት ውስጥ ከ35ቱ 15ቱን ብቻ አሟልታ እንደተገኘችም ተገልጿል፡፡
ቱርክ የህብረቱ አባል ለመሆን ካሟላቻቸው መስፈርቶች መካከል ከአስፈጻሚው አካል ተጽዕኖ ነጻ የሆነ የፍትህ ስርዓት አለመዘርጋት እና የዲሞክራሲ መርሆች አለመግበር ዋነኞቹ ናቸው፡፡
31 አባላት ያለው ኔቶ ጉባኤውን በሊቱንያዋ ቪልኒየስ ከተማ እያካሄደ ሲሆን ጉባኤው የሚካሄድበት ቦታ ለሩሲያ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ ነው ተብሏል፡፡