ቱርክ፤ አሜሪካ በኢስታንቡል የቦምብ ፍንዳታ ያወጣቸውን የሀዘን መግለጫ አልቀበልም አለች
ቱርክ፤ ለኢስታምቡል የቦምብ ጥቃት የኩርድ ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርጋለች
የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትቴር “ቦምቡን ያፈነዳችው ሴት በቁጥጥር ስር ውላለች” ብሏል
ቱርክ ፤ ህገ-ወጥ ነው በምትለው የኩርድ ታጣቂ ቡድን በኢስታንቡል ውስጥ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት ስድስት ሰዎች በመሞታቸው ተከትሎ አሜሪካ ያወጣቸውን መግለጫ እንደማትቀበለው አስታወቀች፡፡
የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ብዙውን ጊዜ ዋሽንግተንን በአንካራ “አሸባሪ” ተብለው ለተፈረጁትና በሰሜናዊ ሶሪያ ለመሸጉት የኩርድ ታጣቂዎች የጦር መሳሪያ ታቀርባለች የሚል ክስ ሲያቀረቡ ይደመጣሉ።
በዚህም በአሁኑ ታጣቂዎቹ ፈጽመውታል ለተባለው ጥቃት አሜሪካ ሀዘን ለመግለጽ የሚያስችል በቂ ምክንያት እንደሌላትና ተቀባይነት እንደሌለው የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሌይማን ሶይሉ በቴሌቭዥን በሰጡት አስተያየት"የአሜሪካን ኤምባሲ የሀዘን መግለጫ መልእክት አንቀበለውም ” ብለዋል፡፡
እሁድ እለት ኢስታንቡል ከተማ ኢስቲካል በሚባለው አውራ ጎዳና ላይ በደረሰ የቦምብ ጥቃት 6 ሰዎች መሞታቸውንና 81 መቁሰላቸው ይታወቃል፡፡
ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም የቱርክ መንግስት ለጥቃቱ ህገ-ወጥ የኩርዲስታን የሰራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) ተጠያቂ አድርጓል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የቦምብ ፍንዳታውን “የሽብር ጠረን” ያለበት “መጥፎ ጥቃት” ሲሉ ጠርተውታል።
በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል የዘጠኝ ዓመቷ ልጅ እና አባት እንዲሁም የ15 ዓመቷ ልጅ እና እናት ይገኙበታል ተብሏል።
የኢስታንቡል ፖሊስ ሰኞ እንዳስታወቀው በድርጊቱ የተጠረጠሩት 46 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።
ከቱርክ ሚዲያ ጋር የተጋራው የፖሊስ ቪዲዮ እንደሚያሳየው ከሆነም ወይንጠጅ ቀለም የለበሰች ሶሪያዊት ወጣት ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዷ ናት፡፡
የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሌይማን ሶይሉ መረጃ ዋቢ በማድረግ አናዶሉ የዜና ወኪል ያሰራቸው መግለጫም “ቦምቡን ያፈነዳችው ሴት በቁጥጥር ስር ውላለች” የሚል ነው።
ዋና ተጠርጣሪዋ ለኩርድ ታጣቂዎች የምትሰራ ሶሪያዊት ነች።
"በእኛ ግኝቶች መሰረት የፒኬኬ አሸባሪ ድርጅት ተጠያቂ ነው" ሲሉ ተናግረዋል ሚኒስትሩ፡፡