ቱርክ በራሷ የሰራችውን የባሊስቲክ ሚሳኤል ለሙከራ ተኮሰች
በጥቁር ባህር ላይ ለሙከራ የተተኮሰው የቱርክ ሚሳኤል 561 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዙ ተገልጿል
ቱርክ ሚሳኤሉን በድብቅ በራሷ ባለሙያዎች ነው የሰራችው ተብሏል
ቱርክ በራሷ የሰራችውን የባሊስቲክ ሚሳኤል ለሙከራ ተኮሰች።
የእስያ እና አውሮፓ አህጉር አዋሳኝ ላይ የምትገኘው ቱርክ በራሷ ባለሙያዎች የተሰራ የባሊስቲክ ሚሳኤል መተኮሷን ብሉምበርግ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ይህ የአጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ለሙከራ ያክል በጥቁር ባህር ላይ ተተኩሶ 561 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዙም ተጠቅሷል።
ሪዜ ከተሰኘችው የወደብ ከተማ የተተኮሰው ይህ ሚሳኤል ቱርክ የራሷን ሚሳኤል በራሷ አምርታ ለመታጠቅ ብዙ ርቀት እንደማይቀራት ማሳያ እንደሆነ ተገልጿል።
ሙሉ ለሙሉ በቱርክ ተመርቷል የተባለው ይህ ሚሳኤል ለሙከራ ከተተኮሰበት ሪዜ ከተማ 561 ኪሎ ሜትር ተጉዞ ሲኖፕ በተባለ ወደብ ጋር አርፏል ተብሏል።
ቱርክ ይህን ባልስቲክ ሚሳኤል ታይፉን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተዘጋጀ ድብቅ ስፍራ ለማምረት ሙከራዎችን ስታካሂድ እንደቆየችም ተገልጿል።
የቱርክ መንግሥት እስካሁን ለሙከራ ስለ ተተኮሰው ባሊስቲክ ሚሳኤል በይፋ መረጃ ያልሰጠ ሲሆን፤ ምርቱ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ለህዝብ የማሳወቅ ፍላጎት የለውም ተብሏል።
በፕሬዝዳንት ረሲፕ ኤርዶሀን የሚመራው የቱርክ መንግሥት ከሶስት ዓመት በፊት ሩሲያ ሰራሽ ሱ-400 የተሰኘ የጸረ ሚሳኤል መሳሪያ መግዛቷ ይታወሳል።
የቱርክ ውሳኔ የኔቶ አባል ሆኖ ከሩሲያ የጦር መሳሪያ የገዛች የመጀመሪያዋ ሀገር ስትሆን በአንካራ ድርጊት የተበሳጨችው አሜሪካ ማዕቀብ ጥላለች።