የስዊድንና ፊንላንድ የኔቶ አባልነት በቱርክ እና ሀንጋሪ ምክንያት መቆሙ ተገለጸ
ሁለቱ የኔቶ አባል ሀገራት ከስዊድንና ፊንላንድ እሚፈልጉት ካልተደረገ በቀር የኔቶ አባልነትን እንደማይቀበሉ ገልጸዋል
ኔቶን በአባልነት ለመቀላቀል ሁሉም ሀገራት የግድ በሀገራቸው ህግ አውጪ ምክር ቤት ማጽደቅን እንደ ግዴታ ተጥሏል
የስዊድን እና ፊንላንድ የኔቶ አባልነት በቱርክ እና ሀንጋሪ ምክንያት መቆሙ ተገለጸ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር በቀጥታ ጦርነት ከጀመሩ ስምንት ወራት ሞልቶታል።
ይሄንንም ተከትሎ በአውሮፓ ህብረት ስር ያሉ ነገር ግን የኔቶ አባል ያልሆኑ ሀገራት ሩስያን በመፍራት ኔቶን በአባልነት ለመቀላቀል በርካታ ሀገራት ጥያቄ አቅርበዋል።
ስዊድን እና ፊንላንድ የመጀመሪያውን የኔቶ አባልነት መስፈርት ካሟሉ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ሲሆኑ ኔቶን ሙሉ ለሙሉ ለመቀላቀል ግን የአባል ሀገራቱን ይሁንታ ማግኘት አለባቸው።
በዚህም መሰረት ከ30ዎቹ የኔቶ አባል ሀገራት መካከል ቱርክ እና ሀንጋሪ እስካሁን የሁለቱን ሀገራት የኔቶ አባልነት አልተቀበሉም
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ስዊድን እና ፊንላንድ የኔቶ አባል እንዲሆኑ በቃል ደረጃ ቢቀቡሉም እስካሁን በሀገራቸው ህግ አውጪ ምክር ቤት እንዲጸድቅ እንዳላደረጉ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
ይሄንንም ተከትሎ የፊንላንድ እና ስዊድን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ሳይሳካ የቀረ ሲሆን ቱርክ እና ሀንጋሪ ከሁለቱ ሀገራት የሚፈልጓቸው ጉዳዮች መኖራቸው ዘገባው ጠቁሟል።
ቱርክ በበኩሏ በፊንላንድ ላይ ጥያቄ ባይኖራትም ስዊድን ግን በአንካራ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ለኩርድ ነጻ አውጪ ፓርቲ አባላት ድጋፍ ታደርጋለች በሚል ክስ አቅርባለች።
ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ቱርክ F-16 የተሰኘው የዋሸንግተን ዘመናዊ የጦር መሳሪያን እንዳትታጠቅ የተጣለባት ማዕቀብ ካልተነሳ የስዊድንን የኔቶ አባልነት እንደማታነሳ ገልጻለች።
ሀንጋሪ በበኩሏ በይፋ የስዊድን እና ፊንላንድን የኔቶ አባልነት ጥያቄ እንደማትቃወም በፕሬዝዳንት ኦርባን በኩል ብታሳውቅም በብዙ ምክንያቶች ሰበብ ጥያቄውን በሀገሯ ምክር ቤት ልታጸድቅ አልቻለችም ተብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ቱርክ እና ሀንጋሪ የሩሲያ ወዳጅ ሀገር መሆናቸው የስዊድን እና ፊንላንድን የኔቶ አባልነት እንዳያጸድቁ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ ዘገባው ጠቁሟል።