የክሪፕቶ ከረንሲ ድርጅት አለቃ የሆነው ተከሳሹ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ይዞ መሰወሩ ተነግሯል
ቱርክ የምናባዊ ገንዘብ (ክሪፕቶ ከረንሲ) አለቃ የነበረውን ግለሰብ መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾችን ሚሊዮን ዶላሮችን አጭበርብሯል በሚል በ11 ሽህ 196 ዓመት እስራት በይናለች።
ፋሩክ ኦዘር የተባለው የ29 ዓመት ወጣት በ2021 "ቶዶክስ ኤክስቼንጅ" የተባለ ድርጅቱ ሲከስር የመዋዕለ ነዋይ አፍሳሾችን ገንዘብ ይዞ ወደ አልቤንያ መሸሹ ተነግሯል።
በወቅቱ ተከሳሹ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የተገመተ እሴት ይዞ እንደተሰወረ የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በሰኔ ወር ለቱርክ ተላልፎ የተሰጠው ኦዘር፤ ህገ ወጥ ገንዘብን ህዊ ለማስመሰል በመሞከር፣ በማጭበርበርና በተደራጀ ወንጀል መከሰሱ ተገልጿል።
በኢስታንቡል የዋለው ችሎት እህትና ወንድሙንም በተመሳሳይ ወንጀል ጥፋተኛ ብሏል።
የቱርክ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች እንደዘገቡት ተከሳሾቹ ለየብቻ በበርካታ ወንጀሎች ብይን የተሰጣቸው ሲሆን፤ ከሁለት ሽህ በላይ ሰዎችን አጭበርብረዋል ተብሏል።
በዚህም ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸው በ11 ሽህ 196 ዓመት በእስራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል።
በቱርክ የሞት ፍርድ በ2004 ከተነሳ በኋል እንዲህ አይነት ረጅም ብይኖች የተለመዱ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
አንካራ ለተዳከመው ገንዘቧ መከላከያ ይሆን ዘንድ ክሪፕቶ ከረንሲን መጠቀም ጀምራለች።
ቶዶክስ በ2017 ተመስርቶ በሀገሪቱ ግዙፍ የምናባዊ ገንዘብ መለዋወጫ ለመሆን በቅቷል።