ቱርክ ለስዊድን የኔቶ አባልነት ድጋፍ የምሰጠው በሽብርተኝነት ላይ እርምጃ ስትወስድ ነው አለች
ስዊድንና ፊንላንድ የገለልተኛ ወታደራዊ አጋርነት ፖሊሲን ቀይረው ባለፈው ዓመት ኔቶን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል
የኔቶ የአባልነት ማመልከቻ በሁሉም የጥምረቱ አባላት መጽደቅ አለበት
ቱርክ የስዊድን ኔቶ አባልነት ጥያቄን ከስቶክሆልም ሽብርተኝነትን የመዋጋት ትብብር ጋር እንደምታያይዘው ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ተናግረዋል።
ስዊድን እና ፊንላንድ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ ባለፈው ዓመት የኔቶ አባልነት ጥያቄ አቅርበዋል። ይህም በቀዝቃዛው ጦርነት የዘለቀውን የወታደራዊ ገለልተኛነት ፖሊሲን ቀይሯል።
የኔቶ የአባልነት ማመልከቻ በሁሉም የጥምረቱ አባላት መጽደቅ አለበት።
የስዊድን ኔቶን የመቀላቀል ጥያቄ ከአንድ ዓመት በላይ የዘገየ ሲሆን፤ ኤርዶጋን በዚህ ወር ከሉታኒያ የጥምረቱ ጉባኤ በኋላ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጥያቄውን ለቱርክ ፓርላማ ለማስተላለፍ ተስማምተዋል።
"የቱርክ ፓርላማ የስራ መርሃ-ግብር የስዊድን የኔቶን አባልነት (ማጽደቂያ) ሂደትን ይወስናል" ሲሉ ኤርዶጋን ተናግረዋል።
"ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር በሚደረገው ትግል እና አሸባሪዎችን አሳልፎ በመስጠት ላይ ተጨባጭ እርምጃዎችን ቢወስዱ ለስዊድን ይጠቅማታል" ብለዋል።
አንካራ እንደ አሸባሪ በምትመለከታቸው ሰዎች ላይ በተለይም የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) አባላት እና በፈረንጆቹ 2016 የከሸፈውን መፈንቅለ መንግስት አስተባብረዋል ያለቻቸውን ሰዎች አሳልፎ ለመስጠት ትብብሯ አነስተኛ ነው ስትል ትከሳለች።
የስዊድን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቅርቡ አንካራ የአሸባሪ ቡድን አካል ናቸው ያለቻቸውን ሁለት የቱርክ ዜጎች ተላልፈው እንዳይሰጡ ከልክሏል።