ታዋቂው የቱርክ ተዋናይ ትምህርት ቤቱን ወደፍርስራሽነት ለውጦታል
ቻላር አርቱግሩል የተባለው ተዋናይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቱን ገዝቶ ያወደመው ይገርፉኝ የነበሩ መምህራንን ለመበቀል ነው ብሏል
ድርጊቱ የተዋናዩን አድናቂዎች በሁለት ጎራ ቢከፍልም ነቀፌታው ጠንከር ማለቱ ተገልጿል
ቱርካዊው ታዋቂ ተዋናይ ቻላር አርቱግሩል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለበትን ትምህርት ቤት ወደ ፍርስራሽነት ቀይሮታል።
አርቱግሩል የልጅነት ትዝታው የታተመበትን ትምህርት ቤት ለማፈራረስ መግዛት ነበረበት።
ተዋናዩ ትምህርት ቤቱን የግሉ ንብረት ያደረገው አድሶ ስራውን ሊያስቀጥለው አልያም አፈራርሶ ቦታውን ለሌላ ልማት ለማዋል አልነበረም።
ዋነኛ አላማው በልጅነቱ ቂም የያዘባቸውን መምህራን መበቀል ነበር።
አርቱግሩል በፈራረሰ ትምህርት ቤቱ ቆሞ የተነሳውን ምስል በኢንስታግራም ገጹ አጋርቷል።
ከምስሉ ጋር አያይዞ በለጠፈው ጽሁፍም ትምህርት ቤቱን ያፈራረሰበትን ምክንያት አስቀምጧል።
“የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ስከታተል አስተማሪዎች ሁሌም ይደበድቡኝ ነበር፤ እናም ትምህርት ቤቱን ገዝቼ አፈራርሸዋለሁ፤ በዚህ ስፍራ ላይ ምንም ግንባታ አላካሂድበትም፤ መጥፎ ትዝታዬ እንደ ህንጻው ሁሉ ፈራርሶ በዚያው ይቀራል” ብሏል ተዋናዩ በጽሁፉ።
ድርጊቱ በልጅነት አዕምሮ የሚቀመጥ መጥፎ ነገርና ቂም በቀላሉ እንደማይሽርና የበቀል እርምጃውም የከፋ እንደሚሆን ማሳያ ነው ተብሏል።
የታዋቂው ተዋናይ ድርጊት አድናቂዎቹን በሁለት ጎራ ከፍሏል።
በመምህራን የሚፈጸሙ ድብደባዎችና በራስ መተማመንን የሚቀንሱ ተግባራት እንዲታይ እድል ፈጥሯል የሚሉት ደግፈውታል።
በርካቶች ግን የተዋናዩ ድርጊት አጠቃላይ የትምህርት ስርአቱን ያላከበረና የበርካታ ተማሪዎችን ትዝታ ያጠፋ ነው በሚል ተችተውታል።
ቻላር አርቱግሩል በበርካታ ፊልሞችና ተከታታይ ድራማዎች በመተወን ከቱርክ ባሻገር በበርካታ ሀገራት ተወዳጅነትን ያተረፈ ሲሆን አለማቀፍ ሽልማቶችንም አግኝቷል።