“ቱርክ በአስፈላጊ ሰዓት ያሳየችውን ወዳጅነት አደንቃለሁ”-ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ ወደ ቱርክ ያቀኑት በፕሬዘዳንት ኤርዶሃን ግብዣ ነው
ሁለቱ ሀራት በወታደራዊ የፋይናንስ ዘርፍ ትብብር ለማድረግ ተስማምተዋል
ቱርክ በአስፈላጊ ሰዓት ያሳየችውን ወዳጅነት እንደሚያደንቁ በአንካራ ጉብንት ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ያሉት በቱርክ እንካራ ከቱርኩ አቻቸው ፕሬዘዳንት ኤርዶሃን ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታኢብ ኤርዶሃን የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቱርክ በአስፈላጊ ሰዓት የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆኗን ማሳየቷን ገልጸዋል፡፡
“እኔን እና ልዑካን ቡድኔን በዛሬው ዕለት በቱርክ በደማቅ አቀባበል ስለተቀበሉን ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋንን አመሰግናለሁ። የፈረምናቸው ስምምነቶች የግንኙነታችንን መጠናከር ያመለክታሉ። ለኢትዮጵያ የልማት እና መረጋጋት ጉዞ ቱርክ የምታደርገውን ድጋፍ አደንቃለሁ።” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
አንካራ እና አዲስ አበባ ከ16 ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የቆየ ወዳጅነት እንዳላቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱም ሀገራት የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ላላት ወዳጅነት ትልቅ ትርጉም እንደምትሰጠውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የገለጹት፡፡ ሁለቱ ሀገራት በውኃ እና በፋይናንስ ዘርፎች በጋር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ ወደ ቱርክ ያቀኑት በፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን ግብዣ መሆኑን የቱርኩ የዜና ወኪል አናዶሎ መዘገቡ ይታወሳል፡፡የቱርክና የኢትየጵያ ግንኙነት ዘንድሮ 125ኛ አመቱን አስቆጥሯል፡፡
ቱርክ ከሰሞኑ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ለኢትዮጵያ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን መግላጿ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ግጭት አሁን ላይ ወደ አጎራባች ክልሎች ተስፋፍቷል፤በግጭቱም በርካቶች መገደላቸውንና በመቶ ሺዎች የሞቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡