ፕሬዘዳንት ኤርዶሃን የአሜሪካንን ጨምሮ የ10 አገራት አምባሳደሮች ቱርክን ለቀው እንዲወጡ አዘዙ
የአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ካናዳ አምባሳደሮች እንዲባረሩ ከተወሰኑት መካከል ዋነኞቹ ናቸው
ዲፕሎማቶቹ እንዲባረሩ የተወሰነው በቱርክ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ነው
ቱርክ የአሜሪካንን ጨምሮ የ10 አገራት አምባሳደሮች አገሯን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ የቱርክ ፕሬዘዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ባስተላለፉት ውሳኔ የአሜሪካንን ጨምሮ የ10 የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮች አንካራን ለቀው እንዲወጡ ተወስኗል።
አምባሳደሮቹ እንዲባረሩ የተወሰነው በፈረንጆቹ 2016 ዓመት ከተካሄደው እና ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጀርባ እጁ አለበት በሚል ተጠርጥሮ ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ ያለ አንድ ግለሰብ ከእስር እንዲፈታ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።
ኦስማን ካቫላ የተሰኘው ይህ የመፈንቅለ መንግስት ተጠርጣሪ በፈረንጆቹ 2013 ዓመት በቱርክ ረብሻ እንዲከሰት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል እና በ2016ቱ የከሸፈው መፈንቅለ መንግስት እጁ አለበት በሚል በእስር ላይ ይገኛል።
ግለሰቡ ባሳለፍነው ሳምንት የፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበረው ሲሆን በአንካራ የሚገኙ የአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ፊንላንድ፣ ስዊድን፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ሆላንድ፣ እና ኒውዝላንድ አምባሳደሮች የፕሬዘዳንት ረሲፕ ኤርዶሀን መንግስት ተከሳሹን በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቅ በጋራ ጠይቀዋል።
የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም አምባሳደሮቹን ጠርቶ ስለጉዳዩ እንዲያብራሩ የጠየቀ ሲሆን ድርጊቱ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው እና በአገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት መሆኑን ጠቅሶ ውድቅ አድርጎታል።
ፕሬዘዳንት ኤርዶሃን በአምባሳደሮቹ ድርጊት መበሳጨታቸውን ገልጸው በአስቸኳይ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መወሰኑን ተናግረዋል።
የአሜሪካ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ በጉዳዩ እስካሁን ያሉት ነገር እንደሌለ ሮይተርስ በዘገባው አክሏል።