ቱርክ በሱዳን የሚገኙ ዜጎቿን በኢትዮጵያ በኩል ልታስወጣ ነው
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መቭሉት ካቩሶግሉ ከኢትዮጵያ አቻችወው ደመቀ መኮነን ጋር በስልክ ተወይይተዋል
በሱዳን የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ሀገራት ዜጎቻቸውን በማስወጣት ላይ ይገኛሉ
ቱርክ በሱዳን የሚገኙ ዜጎቿን በኢትዮጵያ በኩል ለማስወጣት ጥረት እያደረገች መሆኑ ተገለጸ።
ከትናንት በስቲያ እሁድ ከሱዳን የወጡ ዜጎች በኢትዮጵያ ድንበር ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መቭሉት ካቩሶግሉም ከኢትዮጵያ አቻቸው ደመቀ መኮነን ጋር በሂደቱ ዙሪያ በስልክ መምከራቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ በኩል ከሱዳን የሚወጡት ቱርካውያን ከአዲስ አበባ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቀጥታ ወደ ኢስታንቡል እንደሚያመሩ ነው አናዶሉ ያስነበበው።
በሱዳን 12ኛ ቀኑን የያዘው ጦርነት ከፍተኛ ስጋት የገባቸው ሀገራት ዜጎቻቸውን በአውሮፕላን እና በመርከብ እያስወጡ ነው።
ከካርቱም ዜጎቻቸውን በአየር ትራንስፖርት ለማስወጣት ያልተሳካላቸው ሀገራት በየብስ ትራንስፖርት በኢትዮጵያ ድንበር በኩል እያስወጡ እንደሚገኙ አል ዐይን ከምንጮቹ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል።
ሀገራቱ ዜጎቻቸውን በጋላባት-መተማ በኩል በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ በማድረግ ከዚያም ወደ ሀገራቸው እያጓጓዙ ነው ተብሏል።
ቱርክ በይፋ በኢትዮጵያ በኩል ዜጎቿን ለማስወጣት እየተንቀሳቀሰች መሆኑን በማሳወቅ ቀዳሚዋ ብትሆንም በርካታ ሀገራት በዚሁ መስመር ዜጎቻቸውን ከሱዳን እንደሚያስወጡ ይጠበቃል።
በተያያዘ ጋላባት የደረሱ የናይጀሪያ ዜግነት ያላቸው ተማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባት አልቻልንም የሚል ቅሬታን እያሰሙ ነው።
ተማሪዎቹ የናይጀሪያ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ተነጋግሮ ከሱዳን እንዲያስወጣቸውም መጠየቃቸውን የናይጀሪያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኘው የናይጀሪያ ኤምባሲም ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መምከሩና በቀናት ውስጥ ተማሪዎቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እንደሚደረግ ቫንጋርድ የተሰኘው እለታዊ የናይጀሪያ ጋዜጣ አስነብቧል።
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በአሜሪካ አደራዳሪነት ለ72 ስአታት ተኩስ ለማቆም መስማማታቸውም የውጭ ሀገር ዜጎችን ከሱዳን ለማስወጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ያግዛል ተብሎ ታምኖበታል።