“የሱዳንን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ”- ጄነራል ዳጋሎ
ዳጋሎ “90 በመቶ የሱዳን ጦር ከጥቅም ውጪ ሆኗል፤ ከአልቡርሃን ጋር መነጋገር ዋጋ የለውም” ብለዋል
የሱዳን ጦር በበኩሉ “ጦራችን ካርቱምን እየተቆጣጠረና ደህንነቷን እያስጠበቀ ነው” ብሏል
ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤስ.ኤፍ) ተብሎ በሚጠራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ዋና አዛዥ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ “የሱዳንን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ” አሉ።
ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ዙሪያ ከስካይ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ “አሁን ላይ እየተዋጋን ያለነው ከሱዳን ጦር ጋር ሳይሆን ከቅጥረኛ ኃይሎች ጋር ነው፤ ምክንያቱም 90 በመቶ የሱዳን ጦር ከጥቅም ውጪ ሆኗል” ብለዋል።
ዳጋሎ አክለውም፤ “ከዚህ በኋላ ከሱዳን ጦር ዋና አዛዣ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር ተቀምጦ መነጋገር ምንም ዋጋ እንደሌለውና አልቡርሃን ከዚህ በኋላ ያለው አማራጭ እጅ መስጠት ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“ጦርነት አልፈልግም ነበር፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላም እና መረጋጋትን ነው የምመርጠው” ያሉት ዳጋሎ፤ “ወደ ጦርነት እንድንገባ የገፋፋን አልቡርሃን ነው፤ አሁን ግን እጁ ላይ ምንም አልቀረለትም” ሲሉም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የት እንዳሉ የተጠየቁት ሃሜቲ፤ “እኔ የሱዳን ህዝብ አንድ አካል ነኝ፤ ካርቱምን ለቀቄ ወደየትም መሄድ አልችልም፤ እዛው ጦር ግንባር ላይ ነኝ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የሱዳን መከላከያ ሰራዊት በበኩሉ በዛሬው እለት በቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ በኩል ጦርነቱን አስመልክቶ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በሱዳን ያለው ሁኔታ እየተረጋጋ መሆኑን እና የሱዳን ጦር የካርቱም የመኖሪያ አካባቢዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
“የአማጽያኑ አፍ የሆኑ መገናኛ ብዙሃን ከጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን አንስቶ ተመሳሳይ ውሸቶችን እየደጋገሙ ነው” ሲልም የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት አስታውቋል።
የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን ከሱዳን ከማስወጣት ጋር በተያያዘ ከሀገራት መሪዎች ጋር ግንኙነት እየተደረገ መሆኑን እና የማስወጣት ሂደቱ አሁን ባለበት ሂደት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል አባላት ከአማጺው ቡድን ራሳቸውን በማላቀቅ የሱዳንን ጦር እንዲቀላቀሉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፤ ፈጥኖ ደራሽ ኃሉን መልቀቃቸውን ሪፖርት ባደረጉበት እለት ወደ ሱዳን መከላከያ ሰራዊት እንደሚቀላቀሉም የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።