ቱርክ የአሜሪካን የማዕቀብ ዛቻ "ትርጉም የለሽ" በማለት አጣጣለች
የሩሲያ እና የቱርክ ፕሬዝዳንቶች ምጣኔሃብታዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው ይታወሳል
አሜሪካ ቱርክ ከሩሲያ ጋር ካላት ግንኙነት የማትታቀብ ከሆነ ማዕቀብ ሊጠብቃት እንደሚችል አስጠንቅቃለች
ቱርክ ከሩሲያ ጋር ባላት ግንኙነት ምክንያት ከአሜሪካ እየደረሳት ያለውን የማዕቀብ ዛቻ "ትርጉም የለሽ" በማለት አጣጥላለች።
አሜሪካ ከሰሞኑ ከሩሲያ ጋር ባላት ግንኙነት ቱርክን ያስጠነቀቀች ሲሆን፤ አንካራ ከድርጊቷ የማትታቀብ ከሆነ ማዕቀብ ሊጠብቃት እንደሚችል ዋሽንግተን አሳስባለች።
ከሩሲያ ጋር የንግድ ግንኙነቶችን ማድረግ የሚቀጥሉ ከሆነ ማዕቀብ ሊጠብቃቸው እንደሚችል የሚያሳስብ ደብዳቤ ከአሜሪካ ግምጃ ቤት እንደደረሳቸው የቱርክ የንግድና ዘርፍ ማህበራት አስታውቀዋል።
አሜሪካ፤ ሩሲያ እና ቱጃሮች በቱርክ የንግድ ሸሪኮቻቸው በኩል ከተጣለባቸው ማዕቀብ ለመሸሽ እንቅስቃሴዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል ሁኔታዎችን በንቃት እየተከታተለች እንደሆነ አስታወቃለች።
ይህንን ተከትሎም የቱርክ የፋይናንስ ሚኒስቴር ከሀገሪቱ ባለህበቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ማዕቀብ ከተጣለባቸው የሩሲያ አካላት ጋር በተያያዘ የአሜሪካ ማዕቀብ ስጋት ላይ የሚጥል አይደለም ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በቱርክ የንግድ ሰዎች ላይ ስጋት እያሳደረ ያለው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ደብዳቤ “ትርጉም የለሽ ነው” ሲልም አስታውቋል።
የሩሲያ እና የቱርክ ፕሬዝዳንቶች ምጣኔሃብታዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ከወር በፊት በሪዞርት ከተማዋ ሶቺ መስማማታቸው ይታወሳል።
ቱርክ ከሩሲያ ጋር ያላት የወጪ ንግድ መጠን ካሳለፍነው ግንቦት ወዲህ በእጥፍ እየጨመረ ነው፡፡ ከሩሲያ የምታስገባው የነዳጅ መጠንም ጨምሯል፡፡ ነዳጁን በሩብል ለመግዛትም በቅርቡ ተስማምታለች።
ይህን ተከትሎ ባሳለፍነው ግንቦት ወደ አንካራ ጎራ ያሉት የአሜሪካ ግምጃቤት ምክትል ገዢ ስለ ሁኔታው አስጠንቅቀው ነበር፤ በማዕቀብ ስር ካሉ የሩሲያ ተቋማት ጋር ግንኙነት ማድረግ ለማዕቀብ እንደሚዳርግ አሳስበወ ነበር።
ምንም እንኳን የኔቶ አባል ብትሆንም ልክ እንደሌሎች ምዕራባውያን ሁሉ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያልፈለገችው ቱርክ ከሩሲያም ሆነ ዩክሬን ጋር ገለልተኛ መስላ መታየትን መርጣለች።
ይህም በሩሲያ ነዳጅ ላይ ካላት ጥገኝነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ተናግረዋል።