ትዊተር ከአራት ዓመታት እገዳ በኋላ በድጋሚ የፖለቲካ ማስታወቂያዎችን ፈቀደ
ኩባንያው በአስፈላጊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተመሰረቱ ማስታወቂያዎችን እንደሚፈቅድ አስታውቋል
ኢለን መስክ ትዊተርን በጥቅምት ወር መገባደጃ ላይ ከገዙ ወዲህ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው
ትዊተር የማስታወቂያ ፖሊሲውን እንደሚያስተካክል ከገለጸ ከአንድ ቀን በኋላ የማህበራዊ ትስስር መድረኩ በፈረንጆቹ 2019 በፖለቲካዊ ማስታወቂያዎች ላይ የጣለውን እገዳ እንደሚሰርዝ አስታውቋል።
ኩባንያው በአሜሪካ ውስጥ “ምክንያት ላይ የተመሰረቱ ማስታወቂያዎች” ላይ ያለውን ፖሊሲ ላላ እንደሚያደርግና የማስታወቂያ ፖሊሲውን ከቴሌቪዥን እና ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር እንደሚያስተካክል ተናግሯል።
ሮይተርስ እንዳለው መጪው ለውጥ የትዊተርን ፖሊሲዎች ከፌስቡክ ሜታ እና አልፋቤት ዩቲዩብ መድረኮች ጋር በማቀራረብ የፖለቲካ ማስታወቂያዎችን የሚፈቅድ ይሆናል።
የቻይናው ቪዲዮ መተግበሪያ ቲክ ቶክ ግን የፖለቲካ ማስታወቂያዎችን ይከለክላል።
የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያው ለውሳኔው ማብራሪያ ሲሰጥ "በአስፈላጊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተመሰረቱ ማስታወቂያዎች የህዝብ ውይይቶችን እንደሚያመቻቹ እናምናለን" ብሏል።
በትዊተር ላይ የሚፈቀዱት ማስታወቂያዎች እንደ የመራጮች ምዝገባ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ወይም እንደ ቆጠራ ያሉ የመንግስት መርሀ-ግብሮች መሆናቸውን የትዊተር የአመኔታና የደህንነት ኃላፊ አክለዋል።
በፈረንጆቹ 2019 የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ስለ ምርጫዎች የተሳሳተ መረጃ እንዲሰራጭ በመፍቀዳቸው ሰፊ ትችት ካጋጠማቸው በኋላ ትዊተር ማስታወቂያዎችን አግዷል።
ኢለን መስክ ትዊተርን በጥቅምት ወር መገባደጃ ላይ ከተቆጣጠሩ ወዲህ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።
መስክ ትዊተር በሚቀጥለው ዓመት ሦስት ቢሊዮን ዶላር "አሉታዊ የገንዘብ ፍሰት" እንደሚጠብቀው በመግለጽ ወጪን የመቀነስ እርምጃዎችን ከትችት ተከላክለዋል።