ኤለን መስክ ትዊተርን ከገዙ በኋላ በሌሎች ከተሞችም ወጪ ለመቀነስ በሚል የህንጻ ኪራይ መክፈል ማቆማቸው ተነግሯል
ግዙፉ የመረጃ መለዋወጫ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ትዊተር በቢሊየነሩ ኤለን መስክ ከተገዛ በኋላ መነጋገሪያነቱ ቀጥሏል።
ኩባንያው የህንጻ ኪራይ መክፈል ማቆሙም ለክስ ዳርጎታል።
ትዊተር በካሊፎርኒያ ሳንፍራንሲስኮ በሚገኝ ህንጻ ላይ ዋናው ቢሮው ይገኛል።
30ኛ ፎቅ ላይ ለሚገኘው ለዚህ ዋናው ቢሮው መክፈል የነበረበት 136 ሚሊየን ዶላር ኪራይ አለመከፈሉ ነው ክስ ያስመሰረተበት።
የህንጻው ባለቤት ጉዳዩን ወደ ሳንፍራንሲስኮ አካባቢ ፍርድ ቤት ወስድውትም ትዊተር በአምስት ቀናት ውስጥ ኪራዩን እንዲከፍል ተወስኗል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የተሰጠው ውሳኔ ግን ተፈጻሚ አልሆነም ተብሏል።
ኒውዮርክ ታይምስ ባወጣው ዘገባ ትዊተር በሳንፍራንሲስኮ ዋናው ቢሮ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አለም አቀፍ ቢሮዎቹም ለሳምንታት ኪራይ መክፈል ማቆሙን ያሳያል።
ኤለን መስክ ኩባንያውን እንደገዙ በአውሮፕላን ላደረጓቸው ጉዞዎች መፈጸም የነበረባቸው የ197 ሚሊየን ዶላር ክፍያ መዘግየትም ክስ ሊያስመሰርትባቸው ይችላል ነው የተባለው።
መስክ እነዚህን የክስ ጉዳዮች እንዲከታተሉም ከስድስት በላይ ጠበቆችን ከስፔስ ኤክስ ኩባንያዎች ማምጣታቸው ተገልጿል።ትዊተር በአሜሪካዊው ቢሊየነር በ44 ቢሊየን ዶላር ከተገዛ በኋላ በርካታ ሰራተኞቹን አባሯል።
የህንጻ ኪራይ አለመክፈሉም ኩባንያው የገጠመው ቀውስ ማሳያ ተደርጎ ይነሳል።
የኩባንያው ባለቤትና ስራ አስፈጻሚ ኤለን መስክ ግን ትዊተር ኪሳራ ሳያጋጥመው አልቀረም በሚል የሚቀርቡ መረጃዎችን አስተባብለዋል።
የትዊተርን ወጪ ያበዙ ጉዳዮችን ከመቅረፍ ጋር ተያይዞ የታዩት ችግሮች የኩባንያውን ትርፋማነት ማነስ አያመላክቱም ሲሉም ነው የተደመጡት።
ኤለን መስክ በህዳር ወር 2022 ከትዊተር ሰራተኞች ጋር ሲመክሩ ኩባንያው ኪሳራ ሊያጋጥመው እንደሚችል ፍንጭ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።