ትዊተር ለሰማያዊ ባጅ ወይም “ቬሪፊኬሽን” በወር 20 ዶላር ሊያስከፍል ነው
ትዊተር ለሰማያዊ ባጅ ወይም ቬሪፊኬሽን በወር 20 ዶላር ሊያስከፍል ነው፡፡
የዓለማችን የኤሌክትሮኒክስ ተሸከርካሪዎችን አምራች የሆነው ቴስላ ኩባንያ እና ስታርሊንክ የተሰኘው የኮሙንኬሽን ሳተላይት ባለቤት ኤለን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊየን ዶላር ገዝተዋል፡፡
ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ በዓለማችን ካሉ ዋነኛ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል አንዱ የሆነው ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ቢስማሙም የግዢ ስምምነቱ ሳይተገበር ቆይቷል፡፡
ቁልፍ የኩባንያው አመራሮችን በማሰናበት ስራ የጀመሩ ኤለን መስክ የሰማያዊ ባጅ ወይም ቬሪፊኬሽን ለሚፈልጉ የትዊተር ተጠቃሚዎች አዲስ የክፍያ መንገድ እንዲዘረጋ ለሰራተኞቻቸው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
እንደ ኒዮርክ ፖስት ዘገባ ከሆነ ተዊተር ለቬሪፊኬሸን በወር 20 ዶላር ለማስከፈል እቅድ ያወጡ ሲሆን አገልግሎቱም ከፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ከህዳር ሰባት ጀምሮ እንደሚተገበር ተገልጿል፡፡
ኤለን መስክ የሄን ውሳኔ የወሰኑት ከአዲሱ ኩባንያቸው የሚያገኙትን ገቢ በአራት እጥፍ ለማሳደግ በማለም ሲሆን ከዚህ በፊት የሰማያዊ ባጅ ወይም ቬሪፊኬሽን ያላቸው ገጾች በ90 ቀናት ውስጥ ወደ አዲሱ ወርሃዊ ክፍያ ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ ይገደዳሉም ተብሏል፡፡
ከዚህ በፊት የሰማያዊ ባጅ ወይም ቬሪፊኬሽን ያላቸው ገጾች በ90 ቀናት ውስጥ ወደ አዲሱ ወርሃዊ ክፍያ ስርዓት ውስጥ ካልገቡ ግን የተሰጣቸው የሰማያዊ ባጅ እንደሚነሳ ዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ኤለን መስክ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ እየተተገበሩ ያሉት የትዊተር ገቢ ማስገኛ መንገድ እንደማያስደስታቸው ገልጸው አሰራሩን ሙሉ ለሙሉ ሊቀይሩት እንደሚችሉ ተናግረው ነበር፡፡
ትዊተር ከአንድ ዓመት በፊት ለተጠቃሚዎቹ ሰማያዊ ባጅ መስጠት የጀመረ ሲሆን ሀሰተኛ ዜናዎችን ለመከላከል ሲባል አሰራሩን እንደጀመረ በወቅቱ ጠቁሞም ነበር፡፡
የኤለን መስክ ዋነኛ ፍላጎት ትዊተር ሰፊ እና ጤናማ ሀሳቦች በበይነ መረብ ትስስር የመወያያ መድረክ እንዲሆን ማድረግ ነው የተባለ ሲሆን ለዚህ የሚረዱ አሰራሮችን እየዘረጉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በፊት የነበሩ የትዊተር አመራሮች ሀሳቤን በነጻነት እንዳልገልጽ ገድቦኛል ያሉ ሲሆን አሁን ግን ኩባያው በትክክለኛው ሰው እጅ ላይ ወድቋል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ይሁንና ትዊተር ኩባንያ በኤለን መስክ መገዛቱን ተከትሎ ወደ ትዊትር ሊመለሱ ይችላሉ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በፍጹም አልመለስም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡