ሌሎች የተጎዱ ሰላም አስከባሪዎች መኖራቸውም ተነግሯል
በማሊ ተሰማርተው የነበሩ ሁለት ግብጻውያን ሰላም አስከባሪዎች ተገደሉ፡፡
ሰላም አስከባሪዎቹ በመንገዶች ላይ በተጠመደ ቦንብ ፍንዳታ ነው የሞቱት፡፡
አሸባሪዎች ያደረጉት ነው በሚል ግድያውን ያወገዘው የአፍሪካ ህብረት ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል፡፡
ጥቃቱ ከሰሞኑ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመ ነው ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማሊ ተልዕኮም ድርጊቱን በጽኑ አውግዟል፡፡
በጥቃቱ የተጎዱ ሰላም አስከባሪዎች መኖራቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ሰላም አስከባሪዎቹ በጸጥታው ምክር ቤት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለማሳካት በማሰብ በማሊ መሰማራታቸውን የገለጹት የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ኃላፊ ዦን ፔሬ የተጎዱት ቶሎ እንዲያገግሙ ተመኝተዋል፡፡
እንዲህ ዐይነቶቹ ጥቃቶች በጦር ወንጀለኝነት ሊያስጠይቁ እንደሚችሉ ያሳሰቡት የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው የማሊ የሽግግር መንግስት ጉዳዩን አጣርቶ ወንጀለኞችን ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡
ድርጊቱን ያወገዘው የጸጥታው ምክር ቤት ተመሳሳይ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቋል፡፡
ሰላም አስከባሪ ልዑካኑ ከሰሞኑም በሰሜናዊ ማሊ ችግር ገጥሟቸው ነበር፡፡ የሎጂስቲክ ተሽከርካሪያቸው በእሳት ተያይዞ አራት ዮርዳኖሳዊ ሰላም አስከባሪዎችም ተጎድተዋል፡፡