በጊኒ ፕሬዝዳንት ቤተመንግስት አቅራቢያ ከባድ የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተሰማ
በተኩስ ልውውጡ ሁለት ሰዎች ከመጎዳታቸው ውጭ በፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተገልጿል
ተኩሱን የከፈቱት “ያኮረፉ የልዩ ኃይል እና ከፍተኛ የጦር ሰራዊት አባላት ናቸው” ተብሏል
በጊኒ ዋና ከተማ ኮናክሬ ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ በሚገኙበት ቤተመንግስት አቅራቢያ ከባድ የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተሰማ፡፡
በተኩሱ ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውም ተሰምቷል፡፡
የተኩስ ልውውጡ በነማን መካከል የተደረገ ነው ለሚለው እስካሁን ግልጽ የሆነ ነገር ባይኖርም፤ አሁን ላይ በርካታ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎቸ በቤተመንግስቱ አካባቢ መኖራቸውን የአይን እማኞች ነግረውኛል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሮይተርስ በማማዲ ዱምቡያ የሚመሩ የሃገሪቱ ብሔራዊ ጦር አባላት ከረብሻው በስተጀርባ ሳይሆኑ እንዳልቀረ በርካታ ምንጮች እየገለጹ ነው ሲል ዘግቧል።
በተኩስ ልውውጡ በፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም አንድ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡
ከወታደራዊ ምንጮች የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ተኩስ የከፈቱት “ያኮረፉ የልዩ ኃይል እና ከፍተኛ የጦር ሰራዊት አባላት” ናቸው፡፡
ተኩስ ከፍተዋል የተባሉት አንጃዎች የኩርፊያቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ግን እስካሁን አልታወቀም፡፡
አሁን ላይ አብዛኛው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን እና የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት ከሚገኝበት ከካሎም ሰፈር ጋር የሚያገናኘው ብቸኛ ድልድይ የተዘጋ ሲሆን በአከባቢው ብዙ የታጠቁ ወታደሮች እንዳሉ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
እስካሁን ሁለት ንጹሃን እንደተጎዱም ጭምር ተገልጿል፡፡
የካሎም ነዋሪው ኦስማን ካማራ" ወታደሮች ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተመንግስት ሲሄዱ አይቻለሁኝ፤ ከባድ የተኩስ እሩምታም ነበር" ሲል ምስክርነቱ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኮንዴ ባለፈው ጥቅምት ወር አወዛጋቢ የነበረውን ምርጫ በማሸነፍ ጨብጠው የቆዩትን በትረ ስልጣናቸው እንዳስቀጠሉ ይታወቃል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በስልጣን ዘመናቸው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃና እንዲያድግ ማድረጋቸው እንደ ስኬት ቢነሳም ዜጎች ተጠቃሚ አላደረጉም በሚል ሲተቹ ቆይቷል፡፡