በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩትን ክሪስ ኩንን ጨምሮ ሁለት የአሜሪካ ሴናተሮች ወደ ሱዳን ሊያቀኑ ነው
ሴናተሮቹ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ተነግሯል
ሌላኛው ሴናተር ክሪስቫን ሀሎን ከኩን ጋር ወደ ሱዳን ያቀናሉም ተብሏል
የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሴናተሮቹ ክሪስ ኩን እና ክሪስቫን ሀሎን ከሰሞኑ ወደ ሱዳን ያቀናሉ ተባለ፡፡
ሴናተሮቹ በመጪው ሰኞ ወደ ካርቱም ያቀናሉ የተባለ ሲሆን ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌ/ጀነራል አብዱልፋታህ አል ቡርሀን እና ከጠቅላይ ሚኒሰትር አብደላ ሀምዶክ ጋር እንደሚወያዩ የሱዳን የዜና አገልግሎት /SUNA/ ዘግቧል፡፡
ሱና ሴናተሮቹ የሱዳን-አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚጎለብትበትና የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ በሚፈታበት ዙርያ ከተለያዩ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉም ብሏል፡፡
ገዳሪፍ አካባቢ የሚገኘውን ኡም ራኩባ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተነገረው፡፡
መጠለያ ጣቢያው በትግራይ ግጭት ምክንያት የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ተጠልለው የሚገኙበት ነው፡፡
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቅርብ የኮንግረስ አጋር እንደሆኑ የሚነገርላቸው ዴሞክራቱ ሴናተር ክሪስ ኩን ከአሁን ቀደም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በትግራይ እና በሌሎችም ወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው ኢትዮጵያ በቀጠናው የአሜሪካ “ቁልፍ አጋር” መሆኗን ያነሱት ሴናተሩ “በኢትዮጵያ የሚካሄድ የትኛውም ዓይነት አሉታዊ ጉዳይ” እንደሚያሳስባቸው መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
ወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ ከሃገራቸው ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የዓለማቀፍ ድርጅቶች ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን በመጠቆም “ስኬታማ ጊዜ” ማሳለፋቸውን መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡