“በኢትዮጵያ የሚካሄድ የትኛውም ዓይነት አሉታዊ ጉዳይ ያሳስበናል”- ሴናተር ክሪስ ኩንስ፣ የጆ ባይደን መልዕክተኛ
ኢትዮጵያ በቀጠናው የአሜሪካ “ቁልፍ አጋር” መሆኗን ያነሱም ሲሆን “በኢትዮጵያ የሚካሄድ የትኛውም ዓይነት አሉታዊ ጉዳይ” ሃገራቸውን እንደሚያሳስብ ገልጸዋል
መልዕክተኛው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል
ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር እንዲመካከሩ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ አዲስ አበባ የተላኩት ዴሞክራቱ ክሪስ ኩንስ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያዩ፡፡
ክሪስ ኩን እና ልዑካቸው በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በአቶ ደመቀ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
አቶ ደመቀ የህግ ማስከበር ዘመቻውን መነሻ፣ ሂደቱ እና ውጤቱን እንዲሁም በአሁኑ ሰአት ትግራይ መልሶ ስለማቋቋምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በዝርዝር ስለማስረዳታቸውም ነው የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት ለኢቲቪ የተናገሩት፡፡
አምባሳደር ዲና መንግስት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ትግራይ ሄደው እርዳታ ማድረግ እንደሚችሉ፣ ዓለም አቀፍ ሚድያዎች ያለውን ሁኔታ በስፍራው ተገኝተው እንዲዘግቡ መፍቀዱንም ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው ይፈፀማል ተብሎ ለተነሳው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቶ ደመቀ “መንግስት ያለ ምንም ማመንታት ወደ ህግ አቅርቦ የማስጠየቅና የመቅጣት አቅጣጫ ይከተላል” ሲሉ ለልዑካኑ ገለጻ ማድረጋቸውንም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡
አምባሳደሩ “ኢትዮጵያ ልኡላዊት ሀገር እንደመሆኗ መጠን በግዛቷ ውስጥ ለምታከናውነው ማንኛውም አይነት የህግ ማስከበር ዘመቻ ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበልም ጭምር አሳውቃለች”ም ብለዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን “ሱዳን በኢትዮጵያ የፈፀመችውን የድንበር ወረራ ልኡላዊነቷን የሚጋፋ” መሆኑን መግለፃቸውንና “ካለችበት እብሪት ወጥታ ወደ ሰላማዊ መፍትሄ እንድትመጣ አሜሪካ ጫና እንድትፈጥር” መጠየቃቸውንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡ የህዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት የተጀመረውን ድርድር እንዲቀጥል ፅኑ ፍላጎት እንዳላት መግለፃቸውንም ጭምር፡፡
ኢትዮጵያ በቀጠናው የአሜሪካ “ቁልፍ አጋር” መሆኗን ያነሱት ሴናተር ክሪስ ኩን በበኩላቸው “በሀገሪቱ የሚካሄድ ማንኛውም አይነት አሉታዊ ጉዳይ አሜሪካን ያሳስባታል” ብለዋል፡፡
ሴናተሩ በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ነው ያሉት፡፡
አሜሪካ በቅርቡ በትግራይ ለተፈጠረው ቀውስ ድጋፍ የሚሆን የ52 ሚልዮን ዶላር ለመለገስ ቃል መግባቷ የሚታወስ ነው፡፡