በቤተሙከራ የተሰራ ስጋ በአሜሪካ ለገበታ ሊቀርብ ነው ተባለ
የከብቶችን ህዋሳት በመውሰድ በቤተሙከራ የሚበለጽገው ስጋ ጣዕሙ እንደ ዶሮ ስጋ ተወዳጅ ነው ተብሎለታል
በካሊፎርኒያ የሚገኘው አፕሳይድ ፉድስ ኩባንያ በዚህ አመት ስጋውን ለገበያ ለማቅረብም ፈቃድ ማግኘቱ ተነግሯል
በሳይንስ ፊልሞች ላይ ይታይ የነበረው በቤተሙከራ የሚሰራ ስጋ አሁን እውን ሆኗል።
በካሊፎርኒያ የሚገኘው አፕሳይድ ፉድስ የተባለ ኩባንያም ሳይንሳዊ ሂደቶችን ተከትሎ የፈጠረውን ስጋ በአሜሪካ ምግብ ቤቶች ለገበታ ሊያቀርበው መዘጋጅቱን ነው ያስታወቀው።
ከቀንድ ከብቶች ህዋሳትን በመውሰድና የተለያዩ ንጥረነገሮችን በመመገብ በቤተሙከራ የሚያድገው ስጋ ጣዕሙ ከዶሮ ስጋ አይለይም ተብሎለታል።
“በስሎ ሲበላ የዶሮ ጣዕም አለው፤ ነጣ ያለ ቀለሙ እና መሳሳቱ ግን ከከብት ስጋ ይለየዋል” ነው ያሉት የምርት ሂደቱን ተከታትለው ስጋውን የቀመሱት የሬውተርስ ጋዜጠኞች።
በሳይንሳዊ ሂደት የሚመረተው ስጋ ጤናማነትም በአሜሪካ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ተረጋግጦ የሰው ልጆች ይመገቡት ዘንድ ፈቃድ ተሰጥቷል።
አፕሳይድ ፉድስ በያዝነው የፈረንጆቹ አመት በተለያዩ የአሜሪካ ምግብ ቤቶች የቤተሙከራውን ስጋ ለገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅቻለሁ ብሏል።
ኩባንያው ምርቱን በእያንዳንዱ የመሸጫ መደብሮች ውስጥ ለማቅረብም አምስት አመታትን ጠብቁኝ ማለቱን ነው ሬውተርስ የዘገበው።
አፕሳይድ አሁን ባለው አቅም በአመት 400 ሺህ ፓውንድ የሚመዝን ስጋን ነው ማቅረብ የሚችለው።
ይህም ከ106 ሚሊየን ፓውንድ በላይ የስጋ ፍላጎት ላላት አሜሪካ ከቁጥር የሚገባ ባይሆንም፥ ኩባንያው በየአመቱ የሚያደርጋቸው ማስፋፊያዎች የተወሰነ ቢሆንም ክፍተትን እንደሚሞላ ይጠበቃል።
ሌላኛው ተቀማጭነቱን ካሊፎርኒያ ያደረገ “ጎድ ሚት” የተሰኘ ተቋምም እንደ አፕሳይድ ፉድስ ሁሉ የቤተሙከራ ስጋውን ለማቅረብ የአሜሪካ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንን ፈቃድ እየተጠባበቀ ነው ተብሏል።
ሲንጋፖር በሳይንሳዊ ሂደት የሚገኘውን ስጋ ጥቅማ ላይ እንዲውል በመወሰን ቀዳሚዋ ሀገር ናት።