አሜሪካ “ሳያማክሩኝ በዜጎቼ ላይ ምርመራ ጀምረዋል” ባለቻቸው ዓለም አቀፍ ዐቃብያነ ህግጋት ላይ የጣለችውን ማዕቀብ አነሳች
ማዕቀቡ በቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተጣለ ነበር
ውሳኔውን ተከትሎ የተወሰዱ እርምጃዎች “ተገቢና ውጤታማ” እንዳልነበሩ ገምግመናል ብሏል የባይደን አስተዳደር
አሜሪካ “ሳያማክሩኝ በዜጎቼ ላይ ምርመራ ጀምረዋል” በሚል በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ፋጦ ቤንሱዳ ላይ ጥላው የነበረውን ማዕቀብ አነሳች፡፡
ማዕቀቡ በቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተጣለ ነበር፡፡
ሆኖም አዲሱ የጆ ባይደን አስተዳደር ማዕቀቡን አንስቶታል፡፡
ይህንንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒዮ ብሊንከን አስታውቀዋል፡፡
“ውሳኔውን ተከትሎ የተወሰዱት እርምጃዎች ተገቢና ውጤታማ እንዳልነበሩ ገምግመናል ነው” ብሊንከን በመግለጫቸው ያሉት፡፡
አሜሪካ በፋጦ እና በሌሎችም የፍርድ ቤቱ ዐቃብያነ ህግጋት ላይ የጉዞ እና የሃብት እገዳ ማዕቀብን የጣለችው በአፍጋኒስታን ዘመቻ ወቅት የአሜሪካ ወታደሮች የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል አልፈጸሙም የሚለውን በመመርመራቸው ነው፡፡
ሆኖም “በአፍጋኒስታንና ፍልስጤም ጉዳይ ላይ ከፍርድ ቤቱ ተስማማን አልተስማማንም የጣልነውን ማዕቀብ አንስተናል” ብለዋል ብሊንከን፡፡
“ጉዳዩ ከማዕቀብ ይልቅ ከአይ.ሲ.ሲ ሰዎች ጋር በመነጋገር እንደሚፈታ እናምናለን”ም ነው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያሉት፡፡
የታሰቡ ዘርፈ ብዙ ተቋማዊ የሪፎርም ተግባራትን ሃገራቸው እንደምትደግፍም ገልጸዋል፡፡
የማዕቀቡን መነሳት አስመልክተው ፕሬዝዳንት ባይደን ትናንት በማህበራዊ ገጾቻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸው አሜሪካ “ውጤታማ ሆኑም አልሆኑ” የቀደሙ መሪዎቿን እና ዜጎቿን “በፍርድ ቤቱ ከመሳደድ” እንደምትጠብቅ አስታውቀዋል፡፡
የትራምፕ አስተዳደር ባለፈው ዓመት ፍርድ ቤቱ የአሜሪካን ሉዓላዊነት ተጋፍቷል በሚል ማዕቀብ እንደጣለበት የሚታወስ ነው፡፡