ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን በ2022 ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ሊወያዩ መሆኑ ተገለፀ
ውይይቱ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ለማጎልበት በሚያግዙ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱ ያደርጋልም ነው የተባለው
በትራምፕ ዘመን ተቀዛቅዞ የነበረው የአሜሪካ-አፍሪካ ግንኙነት በጆ-ባይደን ጊዜ ወደ ይሻሻላ የሚል ተስፋ ተጥሎበታል
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በፈረንጆቹ 2022 ከአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር የመወያየት እቅድ እንዳላቸው ተሰምቷል።
ከዋይት ኃውስ የተገኘ መረጃ እንደሚያመክተው ከሆነ ፕሬዝዳንት ባይደን ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በሚኖራቸው ውይይት “ዓለም አቀፋዊ ትብብርን እና ጥምረት በመገንባት ላይ” የሚያተኩር ይሆናል ተብሏል።
አሜሪካ ሁለተኛውን የአሜሪካ-አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ እንደምታዘጋጅ በአፍሪካ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያሉት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር አንቶኒ ብሊንከን በናይጄርያ በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
ብሊንክን “ሁለተኛው የአሜሪካ-አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ "ዩናይትድ ስቴትስ እና አፍሪካ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የወደፊት እጣፈንታ ወሳኝ እንደሆኑ በሚታመንባቸው ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ለመምከር እንደ እድል ሆኖ የሚያገልግል” ነው ሲልም ተናግረዋል።
ጉባኤው መቼና የት እንደሚዘጋጅ ግልጽ ያላደረጉት ብሊንከን፤ የመሪዎቹ ጉባኤ “የአሜሪካ-አፍሪካ ትብብር እና ዲፕሎማሲ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ” በማድረግ ረገድ ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት ይሆናልም ብለዋል።
ረዥም ዘመናት ያስቆጠረው የአሜሪካ-እፍሪካ ግንኙነት የተለያዩ ምእራፎት ተሻግሮ በተመረጡ የትብብር ማእቀፎች እያደገ የነበረ ቢሆንም በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመን “ዜሮ በሚባል ደረጃ” ተቀዛቅዞ አስጊ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር የውጭ ግንኙነት ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት ሲያነሱት የነበረ ጉዳይ ነው።
የአሜሪካ-አፍሪካ ግንኙነት ኩፉኛ እያሽለቆለ ቢመጣም፤ የፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን አስተዳዳር ወደ ስልጣን መምጣት በሁለትዮሽ ግንኙነቱን ወደ አዲስ ምእራፍ ሊሸጋገር የሚችልበት ተስፋ ተጥሎበታል።
ጆ-ባይደን እንደፈረንጆቹ የካቲት 2021 የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን በማስመልከት ባደረጉት የመጀመርያ ንግግር “አሜሪካ ፊቷን ወደ አፍሪካ አዙራለች” በማለት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቃቸው ይታወሳል።