ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ስልጣናቸውን በጊዜያዊነት ለምክትላቸው ሊያስረክቡ ነው
ፕሬዘዳንቱ ስልጣናቸውን የሚያስረክቡት ለህክምና ማደንዘዣ ከወሰዱ በኋላ በሰመመን ውስጥ ለሚሆኑባቸው ጊዜ ነው
ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ለዛሬ የሆድ እቃ ህክምና ቀጠሮ ይዘዋል
ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ስልጣናቸውን በጊዜያዊነት ለምክትላቸው እንደሚያስረክቡ ተገለጸ።
የ78 ዓመቱ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት በዋልተር ሪድ የህክምና ማዕከል የሆድ እቃ ህክምና ክትትል ለማድረግ ቀጠሮ እንዳላቸው የነጩ ቤተ መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪ አስታውቋል።
በዚህም ምክንያት ፕሬዘዳንቱ ህክምናውን ለመከታተል ህመም መቀነሻ በሚል በሀኪሞች የሚሰጣውን ማደንዘዣ ከወሰዱ በኋላ በሚኖሩት የሰመመን ጊዜያት ውስጥ አገሪቱን የመምራት ሃላፊነት ለምክትላቸው ካማላ ሀሪስ እንደሚሰጡ ተገልጿል።
የፕሬዘዳንት ባይደን የዛሬው የህክምና ቀጠሮ ከዚህ በፊት ያልተያዘ ሲሆን ቀጠሮው በድንገት የሆነ እንደሆነ ዘገባው አክሎ የገለጸ ሲሆን ህክምናው የአንጀት ካንሰር መሆን አለመሆኑን ለመለየት እንደሆነም ገልጿል፡፡
በአሜሪካ የፕሬዘዳንትነት ታሪክ በፈረንጆቹ ከ2002 እስከ 2007 ዓመት ውስጥ ስልጣነ ላይ የነበሩት ፕሬዘዳንት ደብሊው ቡሽ ለህክምና ክትትል ሆስፒታል በገቡበት ወቅት ስልጣናቸውን ለምክትላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ አሳልፈው ሰጥተው ነበር።
በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ ምክትል ፕሬዘዳንት ካማላ ሀሪስ ለተወሰኑ ሰዓታት አሜሪካን በፕሬዘዳንትነት ስልጣን የመሩ የመጀመሪያዋ እንስት ይሆናሉ ተብሏል።
የነጩ ቤተ መንግስት ፕረስ ዋና ጸሃፊ ጄን ሳኪ እንዳሉት የፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የህክምና ሙሉ ሪፖርት ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከጆ ባይደን ጋር ተመሳሳይ የህክምና ቀጠሮ የነበራቸው ቢሆንም ስልጣናቸውን ለምክትላቸው ማይክ ፔንስ ላለማስረከብ ሲሉ ማደንዘዣ አልወሰዱም ብለው ነብር።
ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዘዳንትነት የምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት በወቅቱ ተቀናቃኛቸው የነበሩትን እና የአሁኑን የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዘገምተኛ ነው የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መግባት አለበት የሚሉ ትችቶችን የሰነዝሩባቸው እንደነበር አይዘነጋም።
በዚህ ሳምንት ፖለቲኮ የተሰኘው የቴሌቪዥን ሾው በሰራው የዳሰሳ ጥናት 40 በመቶ አሜሪካዊያን ፕሬዘዳንት ባይደን ጤነኛ ናቸው ብለው የሚያምኑ ሲሆን 40 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ፕሬዘዳንቱ ጤነኛ መሆናቸውን ተቃውመዋል ሲል ሲ.ኤን.ቢ.ሲ ዘግቧል።