ጆ ባይደን ኢትዮጵያን ከአሜሪካ ንግድ ችሮታ (አጎአ) ማስወጣታቸውን ለኮንግረሱ አሳወቁ
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያን መሰረዛቸውን አስመልክቶ ለአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ደብዳቤ ጽፈዋል
ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን ነው ከአሜሪካ ንግድ ችሮታ (አጎአ) ሰረዙት
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ተጠቃሚ ከነበረችበት የአሜሪካ የንግድ ችሮታ (አጎአ) ማስወጣታቸውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ማሳወቃቸውን ኋይት ሃውስ ገለጸ።
ኢትዮጵያ ከንግድ ችሮታው እንዲትወጣ ፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ የጻፉት ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጋር ተያይዞ መሆኑንም ኋይት ሃውስ አስታውቋል።
ዋሸንግተን፤ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ጥልቅ ውይይቶች ተደርገው እንደነበር ገልጻለች።
ጆ ባይደን ከኢትዮጵያ በተጨማሪም ጊኒ እና ማሊም ከአሜሪካ የንግድ ችሮታ (አጉአ) እንዲወጡ ደብዳቤ መጻፋቸውንም ኋይት ሃውስ አስታውቋል።
ሀገራቱ ይህ የተወሰነባቸው የአሜሪካን ፍላጎቶች ማሟላት ባለመቻላቸው መሆኑንም አሜሪካ ገልጻለች።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪና ዋና የንግድ ተደራዳሪ አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ከሰሞኑ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ “በእኛ እምነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የአጎአ ተተቃሚ መሆን የምንችለው አሁን ነው” ብለው ነበር።
ከሰሞኑ አል ዐይን አማርኛ ኢትዮጵያ ይህንን የንግድ ችሮታ እንዳትጠቀም ቢወሰን የተዘጋጁ አማራጮች እንዳሉ አቶ ማሞን ጠይቆ ነበር።
ከፍተኛ አማካሪው አቶ ማሞ ለኢትዮጵያ አምራች ዘርፍ ሌላ አማራጭ የገበያ ዕድሎችም የማመቻቸት እንዲሁም የማምረቻ ወጭያቸው እንዲቀንስ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸው ነበር።
አጎአ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገሮች የአሜሪካ መመንግስት የሚሰጠው ከቀረጥና ከኮታ ነጻ የንግድ ችሮታ ሲሆን በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ዘመን የተፈረመ መሆኑ ይታወሳል።
20 ዓመት ያለፈው ይህ የንግድ ችሮታ እ.ኤ.አ 2025 እንደሚያበቃ እየተነገረ ቢሆንም የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ቅድመ ሁኔታ አላሟላችም በሚል የንግድ ችሮታውን እንዳታገኝ የሚሰሩ አካላት እንዳሉ መንግስት መግለጹ ይታወሳል።