የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶማሊያ የነበረው የአሜሪካ ጦር ከሞቃዲሾ እንዲወጣ ማዛቸው ይታወሳል
አሜሪካ ጦሯ በድጋሚ በሶማሊያ እንዲሰማራ ወሰነች፡፡
ሮይተርስ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ አሜሪካ በድጋሚ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ለመላክ ወስናለች፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አልሻባብ ተዳክሟል በሚል 700 የአሜሪካ ጦር አባላት ሶማሊያን ለቀው እንዲወጣ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አልሻባብ በሶማሊያ እያደረሰው ያለው የሽብር ድርጊት እየጨመረ መጥቷል በሚል የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔን እንደሻሩ ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ውሳኔ አዲስ ፕሬዝዳንት ለመረጠችው ሶማሊያ ጋር አዲስ ግንኙነት ለመመስረት ማሰቧን እንደሚያሳይ ነው የተነገረው፡፡
ሶማሊያን ለቀጣዮቹ 5 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የተመረጡት ሀሰን ሼክ ሞሃመድ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ወዳጆች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡
“ሰላም የሰፈነባት እና ከዓለም ጋር ሰላም ያላት ሀገር ለማድረግ እሰራለሁ”- አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት
አልሻባብ በሶማሊያ ዋነኛ የጸጥታ ስጋት ሲሆን በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት ከ19 ሺህ በላይ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጣ ጦር በሞቃዲሾ የሀገሪቱን ጦር በማገዝ ላይ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ ከ500 ያነሰ ቁጥር ያለው የአሜሪካ ጦር በሶማሊያ ያለ ሲሆን በተመረጡ የአልሻባብ ይዞታዎች ላይ የአየር ላይ ጥቃቶችን በማድረግ ላይ እንደሆነ ዘገባው አክሏል፡፡
አልሻባብ በሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተካሂዶ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዳይካሄድ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ተደጋጋሚ የሽብር ድርጊቶችን ቢያካሂድም ምርጫው ባሳለፍነው እሁድ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ሶማሊያ ከአልሻባብ የሽብር ጥቃት በተጨማሪ ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ እየተፈተኑባት ይገኛሉ፡፡